ቢሮው በአነስተኛ ቦታ በቴክኖሎጂ የታገዘ የከተማ ግብርና ልማት እያካሄደ ነው

44

ባህር ዳር (ኢዜአ) ነሐሴ 12/2014--- የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሞዴል የሆነ በአነስተኛ ቦታ በቴክኖሎጂ የታገዘ የከተማ ግብርና ልማት እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው ለኢዜአ እንዳሉት የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ የሚቻለው በአርሶ አደሩና በሰፋፊ የእርሻ ማሳዎች ብቻ አይደለም።

"ምርታማነትን ለማሳደግ የቦታ ስፋትና ጥበት እንደማይገድብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በቤተ መንግስት ግቢ የለማው የጓሮ አትክልት ጥሩ ማሳያ ነው" ብለዋል።

አነስተኛ የጓሮ ቦታዎችን በመጠቀም ጭምር የግብርና ምርትን ማሳደግ እንደሚቻል የገለጹት ኃላፊው፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሞክሮ በመውሰድ በቢሮው ግቢ ውስጥ ሞዴል የሆነ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።  

በቦታ ጥበት ሳይገደብ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን ባለው አነስተኛ ቦታ ላይ እያለማ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡

ዶክተር ኃይለማርያም እንዳሉት ቢሮው የከተማ ግብርናን ልማት እያካሄደ ያለው የምግብ ዋስትናን በሚያረጋግጥ መልኩና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ነው።

"ልማቱም ለሌሎች ተቋማትና ለከተማ ነዋሪ ተሞክሮ ሊሆን በሚችል መልኩ እየተከናወነም" ይገኛል ብለዋል።

እንደእሳቸው ገለጻ የከተማ ምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ባለ አነስተኛ ቦታ የጓሮ አትክልትን አልምቶ መጠቀም ያስፈልጋል።

የግብርና ምርት እጥረት ሲኖር የከተማ ነዋሪ ግንባር ቀደም ተጎጂ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ኃይለማርያም፣ የከተማ ግብርናን በማስፋፋት ከተሜነትን ከምግብ ዋስትና ጋራ ማረጋገጥ እንደሚቻል ገልጸዋል።

ቢሮው ባለው አነስተኛ ቦታ፣ በመሰላልና በግድግዳ ላይ ጭምር እያለማ ያለውን የጓሮ አትከልት በቀጣይ ለተቋማትና ለህብረተሰቡ በተሞክሮነት የሚያሰፋበትን ፕሮግራም እንደሚያመቻችም ገልጸዋል።

"ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚቻለው በአርሶ አደሩና በሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ብቻ አይደለም" ያሉት የቢሮ ሃላፊው፣ በከተሞች ባለ አነስተኛ ቦታ የቤተሰብ ምግብ ፍጆታን ማሟላት እንደሚቻልም አስገንዝበዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም