የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሴቶች በሀገራዊ የምክክር ሂደት ንቁ ተሳታፎ እንዲያደርጉ እየሰራ መሆኑን ገለጸ

87

አዳማ፣ ነሐሴ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሴቶች በሀገራዊ የምክክር ሂደት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ በመሆን በሀገረ መንግስት ግንባታ ውስጥ የሚናቸውን እንዲጫወቱ እየሰራ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ከክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የሴቶች አደረጃጀት አመራሮች ጋር በሀገራዊ ምክክሩ የሴቶች ተሳትፎ ሁኔታ ላይ ለመምከር ዛሬ በአዳማ ከተማ መድረክ አዘጋጅቷል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ እንደገለጹት፤ ሴቶች በሀገር ግንባታ ሂደት ጉልህ ሚና እንዲኖራቸው፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ በሀገራዊ ምክከር ኮሚሽኑ ንቁ ተሳታፊ መሆን አለባቸው።

የሴቶች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው ሁሉንም በማሳተፍ ችግሮች በዘላቂነት በመፍታት እንደሆነ ገልጸው፤ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት መገንባት የሚቻለውም በሁሉም ተሳትፎ እንደሆነ አመልክተዋል።

ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትህ፣ ልማትና እድገት የዳበረባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ሴቶች በሀገራዊ የምክክር ሂደት ተሳትፎቸው በየደረጃው ሲረጋገጥ እንደሆነ ገልጸዋል።

በምክክር ኮሚሽኑ መድረኮችና ሂደቶች ውስጥ ሴቶች ሚናቸውን እንዲወጡ ከአደረጃጀቶች፣ ማህበራዊ መዋቅሮችና ከተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ሴት አባላትና አመራሮች ጋር ሚኒስቴሩ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የሴቶችን ጥያቄዎችና ሐሳቦች በሀገራዊ ምክክሮች ላይ በተገቢው መንገድ እንዲቀርቡና ምላሽ እንዲኖራቸውም በየደረጃው ካሉት የሴት አደረጃጀቶች ጋር እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በዚህም ሴት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የሴቶች አደረጃጀቶች የማንቃትና የማስተባበር ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በሚኒስቴሩየሴቶች ማብቃት መሪ ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ወይንሸት ገለሶ ሴቶችን በአቅም፣ ክህሎት፣ እውቀትና አመለካከት ለማዘጋጀት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም