የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቀጣይ ዓመት ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭና እና ከተለያዩ ገቢዎች 43 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዷል

24

ነሃሴ 12/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2015 በጀት ዓመት ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭና እና ከተለያዩ ገቢዎች 43 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ እቅድ መያዙን አስታወቀ።

የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሽፈራው ተሊላ በ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና በ2015 ዕቅድን የተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በተያዘው 2015 በጀት ዓመት ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭና እና ከተለያዩ ገቢዎች 43 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ እቅድ ተይዟል ብለዋል።

May be an image of 6 people, people sitting, people standing and indoor

በዚህም ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 33 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከልዮ ልዮ ገቢዎች አንጻር ከማያገለግሉ እቃዎች ሽያጭና ከቆጣሪ ማስቀጠያ እና ከአገልግሎት ክፍያ 9 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ እቅድ ተይዟል ነው ያሉት።

በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን አዳዲስ ደምበኞች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል አገልግሎቱ በተጠናቀቀው 2014 በጀት ዓመት 20 ነጥብ 94 ቢሊዮን ብር ከኃይል ሽያጭ ማግኘቱንም ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ 23 ነጥብ 84 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 20 ነጥብ 94 ቢሊዮን ብር ከሀይል ሽያጭ ያገኘ ሲሆን ይህም የዕቅዱን 88 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ከአዳዲስ ደምበኞች የኤሌክትሪክ መስመር ማስቀጠያ 6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር እና ከአረጀ ንብረት ሽያጭ 113 ነጥብ 13 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በተጠናቀቀው ዓመት 367 ሺህ 466 ደምበኞች የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

204 አዳዲስ ከተሞች እና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሲሆኑ አጠቃላይ የደምበኞች ብዛት 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን መድረሱንም ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ዲስትሪብዩሽን መልሶ ግምባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት 99 ነጥብ 25 በመቶ መድረሱንና የወላይታ ሶዶ፣ ሐረር፣ ሻሸመኔ፣ ደብረማርቆስ፣ ጎንደር እና ኮምቦልቻ ስርጭት መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት አፈጻጸም 69 ነጥብ 7 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የስነ-ምግባር ጥሰት በፈጸሙ 1 ሺህ 50 አመራሮችና ሰራተኞች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውም አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱ ለሲዳማና ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽህፈት ቤቶች መቋቋማቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት 11 ሪጅኖች፣ 26 ዲስትሪክቶች፣ 554 የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት እና ከ5 ሺህ 838 በላይ ሳተላይቶች አደራጅቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም