ቀጥታ፡

ሠራዊቱ የአገርን ሰላምና የሕዝብን ደኅንነት ለማረጋገጥ ከሚያደርገው አኩሪ ተጋድሎ ጎን ለጎን የሕዝብ ወገንተኝነቱን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል - ዶክተር አብርሃም በላይ

ነሃሴ12/2014/ኢዜአ/ የአገር መከላከያ ሠራዊት የአገርን ሰላምና የሕዝብን ደኅንነት ለማረጋገጥ ከሚያደርገው አኩሪ ተጋድሎ ጎን ለጎን የሕዝብ ወገንተኝነቱን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ።

ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው 64 ግለሰቦች የሚውል ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታን ለማስጀመር በአዲስ አበባ ከተማ የመሰረት ድንጋይ በተጣለበት ወቅት ነው።

የሚገነቡት ቤቶችም በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቁና በዝቅተኛ ወጪ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አማካኝነት በተገጣጣሚ ቴክኖሎጂ ግንባታ እንደሆነ ተገልጿል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ፤ የአገር መከላከያ ሠራዊት በመስዋዕትነቱ የአገርን ሰላም ለማረጋገጥ ሌት-ተቀን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

May be an image of 1 person and standing

ሠራዊቱ የአገርን ሰላም ለማረጋገጥ ከሚያከናውናቸው ተግባራት ጎን ለጎንም የዜጎችን ችግር በቅርበት የሚፈታበትን አማራጭ በመጠቀም ሕዝባዊነቱን በተግባር እያረጋገጠ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዜጎች የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ በሚያጋጥማቸው ቦታ ሁሉ የዜጎችን ሕይወት በማዳን የሕዝብ አለኝታ እንደሆነ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ሠራዊቱ በተለያዩ ጊዜያት አቅመ ደካማና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የመኖሪያ ቤት ግንባታም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለዜጎች እንዲተላለፍ የቅርብ ክትትል እንደሚደረግበት አረጋግጠዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መለሰ አለሙ፤ ኢትዮጵያ ፈተናዎቿን በማሸነፍ ታላላቅ የልማት ሥራዎችን ከግብ በማድረስ ብልጽግናዋን እያረጋገጠች ነው ብለዋል።

May be an image of 1 person

የከተማ አስተዳደሩም የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የቤት አቅርቦቱን ማሳደግ ጨምሮ የነዋሪውን ችግር ለመቅረፍ ሰፊ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የመከላከያ ሚኒስቴርም የሚያስገነባው የመኖሪያ ቤት ሕንፃ አቅመ ደካማና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ችግር በመፍታት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ  ነፃነት ዳባ፤ ባለፉት 60 ቀናት በክፍለ ከተማው የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

ከእነዚሁ የልማት ሥራዎች መካከልም 400 በላይ የሚሆኑ የአቅመ ደካማና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖችን ቤት በማደስ ማስተላለፍ እንደተቻለም ገልጸዋል።

የመከላከያ  ሚኒስቴርም አቅመ ደካማና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች የመኖሪያ ቤት ግንባታ መጀመሩን አመስግነው፤ ቤቱ ሲጠናቀቅም የዜጎችን ችግር በመፍታት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም