ቀጥታ፡

ዘጠነኛው ''ስለ ኢትዮጵያ'' መድረክ የፎቶ አውደ ርዕይ በጎንደር ከተማ መካሄድ ጀመረ

ጎንደር ነሐሴ 12 ቀን 2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያዘጋጀው 9ኛው ''ስለ ኢትዮጵያ'' መድረክ የፎቶ አውደ ርዕይ በጎንደር ከተማ መካሄድ ጀመረ፡፡

በአውደ ርእዩ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ፣የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሃመድ እድሪስ፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ጌትነት ታደሰ፣ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በ1950ዎቹና 60ዎቹ ወቅት የነበሩ የኢትዮጵያ ወሳኝ ሁነቶችና በታሪክ ሂደቶች የተከሱቱ የህዝብ ጥያቄዎችን የሚያመላክቱ ፎቶዎች በአውደ ርዕዩ ለእይታ ቀርበዋል፡፡

ለሀገር ሉአላዊነት የተከፈሉ መስዋእትነቶች እንዲሁም የኢትዮጵያን እምቅ የቱሪዝም ሀብቶችና ገጸ በረከቶች የሚመለከቱ ጉዳዮች በፎቶ አውደ ርእዩ መካተታቸው ተገልጿል፡፡

ከፎቶ አውደ ርዕዩ ቀጥሎም ''ስለኢትዮጵያ'' ኢትዮጵያውያን የሚመክሩበት ውይይት የሚካሄድ ሲሆን ''የሚዲያ ሚና_ስለ ኢትዮጵያ'' በሚል ርእስ የመጀመሪያው የፓናል ውይይት ይካሄዳል፡፡

''ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትሻገራለች'' በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው የፓናል ውይይት ደግሞ በሀገሪቱ ፈተና ድልና ተስፋ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከዚህ ቀደም በጅጅጋ፣ ድሬዳዋ፣ ሀረር፣ ሃዋሳ፣ አርባ ምንጭ፣ ጅማ፣ አዳማና ደሴ ከተሞች ተመሳሳይ የፎቶ አውደ ራዕይና የፓናል ውይይት ማካሄዱ ይታውቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም