በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ 101 የተለያዩ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ተመረቁ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ 101 የተለያዩ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ተመረቁ

አዲስ አበባ ነሀሴ 11/20214 በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ 101 የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ተመረቁ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ፕሮጀክቶቹ ተመርቀዋል፡፡
በዛሬው መርሃ ግብር 101 የተለያዩ ፕሮጀክቶች የተመረቁ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 47ቱ መንግስት በመደበው 400 ሚሊዮን ብር የተገነቡ ናቸው ፡፡
ቀሪዎቹ 54 ፕሮጀክቶች በህብረተሰብ ተሳትፎ የተሰሩ የመንገድ፣ የፍሳሽ ማስወገጃና የማስዋብ ስራዎች መሆናቸው ተገልጿል።
በዚሁ የልማት ክንውን 19 የመማሪያ ክፍሎች፣ የአስተዳደር ሕንፃዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ እና የወጣቶች ስብዕና መገንቢያ ማዕከላት ተሰርተዋል።
የላቦራቶሪ እና የመድሃኒት አገልግሎት መስጫ፣ የቤተ መፃሕፍት ግንባታና እድሳት፣ የሼዶች ግንባታና እድሳት፣ እንዲሁም አምስት የማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ ማዕከላት ተገንብተዋል።
ምክትል ከንቲባው ጃንጥራር በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት "ከሰራናቸው ይልቅ ገና የምንሰራቸው ይበዛሉና የመዲናችን ነዋሪዎች ከጎናችን በመሆን የምታደርጉትን ድጋፍ አጠናክራችሁ ቀጥሉ" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለፕሮጀክቶች ፍጻሜ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበው ቀጣይም የትምህርት፣ የጤና፣ የከተማ ግብርና፣ የጽዳት፣ ውበትና ሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ አተኩሮ ይሰራል ሲሉ አረጋግጠዋል።