ለውጭ ገበያ የሚቀርብ የቅባትና የጥራጥሬ እህሎችን ያለአግባብ አከማችተው በሚገኙ ላኪዎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል-የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ለውጭ ገበያ የሚቀርብ የቅባትና የጥራጥሬ እህሎችን ያለአግባብ አከማችተው በሚገኙ ላኪዎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል-የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር
ነሐሴ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ)ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የቅባትና የጥራጥሬ እህሎችን ያለአግባብ በመጋዘን የሚያከማቹ ላኪዎች ላይ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በቅባትና ጥራጥሬ ዘርፍ ላይ የወጪ ንግድ የ2014 በጀት ዓመት አፈፃፀምና የ2015 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
ባለፈው በጀት ዓመት 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ከወጪ ንግድ የውጭ ምንዛሬ መገኘቱ ተገልፆ፣አፈፃፀሙ አገሪቷ ከነበረችበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የሚበረታታ መሆኑ ተወስቷል።
ባለፉት ዓመታት የወጪ ንግድ አፈፃፀም ዕድገት እያሳየ ሲሆን በቅባትና ጥራጥሬ እህሎች ዘርፍ ግን አሁንም መሻሻል እንዳለበት ተገልጿል።
የቅንጅታዊ አሰራር ጉድለት፣ ቴክኖሎጂ መር አገልግሎት አለመኖር፣ የአማራጭ ገበያ ፕሮሞሽን ስራ ጉድለት፣ክትትልና ቁጥጥር ማነስ፣ሕገ ወጥነትና ኮንትሮባንድ የዘርፉ ተግዳሮቶች ነበሩ ተብሏል።
ዓለም አቀፍ ገበያ መቀዛቀዝ፣ የገዥ አገራት መስፈርት ተለዋዋጭነትና ላኪዎች የገዥ አገራትን መስፈርት ያለማሟላት፣ ያለአግባብ የምርት ክምችት፤ያልተገባ የአገር ውስጥ ገበያ ፍለጋና የምርት ጥራት ማነስ የዘርፉ ችግሮች እንደሆኑም ተወስቷል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ፤ በ2015 በጀት ዓመት በአጠቃላይ ከወጪ ንግድ የተያዘውን 5 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ለማሳካት በተለይም የወጪ ንግዱን 72 በመቶ በሚይዘው የግብርናው ዘርፍ ላኪዎች ትልቅ ሃላፊነት ይጠብቃቸዋል ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት በተለይም የግብርና ምርቶችን አይነትና በመጠን በመጨመር ቅባትና ጥራጥሬ እህሎች ኤክስፖርት ብቻ 595 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ግኝት መታቀዱን ገልጸዋል።
ወደ ውጭ መላክ ያለበት ምርት ከአምራቹ ተሰብስቦ በሶስት ወራት ውስጥ ወደ ውጭ መላክ ቢኖርበትም አሁን ላይ የሚስተዋለው ግን ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመት እንደሚከማች ገልጸዋል።
በአዲሰ አበባና በዙሪያው ባሉ ከተሞች ፍተሻ ተደርጎ በፍጥነት እንዲላኩ አቅጣጫ ቢሰጥም አሁንም ቢሆን በላኪዎች መጋዘን ያለውን ረጂም ጊዜ የዘለቀ ከፍተኛ የምርት ክምችት ማቃለል እንዳልተቻለ ተናግረዋል።
ምርቱ በወቅቱ ለውጭ ገበያ ባለመቅረቡ ለምርት ጥራት መቀነስና አገሪቷ ማግኘት ያለባትን የውጭ ምንዛሬ በወቅቱ እንዳታገኝ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ላኪዎች ምርታቸውን በወቅቱ ለዓለም ገበያ ማቅረብ እንደሚገባቸው ነው ያሳሰቡት።
የመድረኩ ተሳታፊ ላኪዎች እንዳሉትም ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች በከፊል ያለቀላቸው ቢሆኑ የውጭ ምንዛሬ መጠን ብቻ ሳይሆን የወጪ ምርቶችን መጠንም ማሳደግ እንደሚቻል ገልጸዋል።
በወጪ ንግድ ዘርፍ እየተካሄዱ ያሉት የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች እንዲፋጠኑ፣የምርት አይነት ስያሜ ጉዳይ፣ በቱሪስት ቪዛ ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ምርቶችን በሚልኩ ደላሎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ለምርት ጥራት መጓደል መንስኤ የሆነው የምርት ክምችት ችግር መቀረፍ እንዳለበትና ለክምችቱ መንስኤ የሆኑ ከውጭ ምንዛሬ ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል ሕገ ወጥነት ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ፣በጎ የሰሩት ላይ ደግሞ የማበረታቻ ርምጃዎች እንዲረጉ ጠይቀዋል።
ሚኒስትር ዴዔታው አቶ ካሳሁን ጎፌ፤ በበጀት ዓመቱ ሕገ ወጥነትን መከላከል በተለይም የአገር ገጽታ የሚያጠለሹና የግብይት ስርዓቱን የሚያውኩ አካላት ላይ ጠንካራ ርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
ላኪዎች ወደ ሚኒስቴሩ ጉዳይ አስፈጻሚ መላክ ሳይሆን ቀርበው ችግራቸውን ማስረዳትና አብሮ መስራት እንዳለባቸው ገልጸው፤ ለውጤታማ ላኪዎችም ልዩ ድጋፍና ማበረታቻ እንዲሚሰጥ ገልጸዋል።
ጥሩ አፈጻጸም ካላቸው ላኪዎች የጋራ ኮሚቴ በማዋቀር በየጊዜው ተቀራርቦ መወያየትና ውሳኔዎችን በጋራ መወሰን እና ችግሮችን በመፍታት ይሰራል ብለዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥና አሰራር ስርዓትን ማዘመን፤ የምርት መዳረሻ ማስፋትና የላኪዎችን ያለአግባብ ውድድርን ማስቀረትና ለቅሬታ አቀራርብ ስርዓትን መዘርጋት ላይ በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያን ጨምሮ ከሌሎች መንግስታዊ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።