በሰው ህይወትና ንብረት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለማስቆም ጠንካራ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በሰው ህይወትና ንብረት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለማስቆም ጠንካራ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል
አዲስ አበባ መስከረም 7/2011 የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴና ምክር ቤት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለማስቆም ጠንካራ እርምጃ ለመወሰድ ግምገማ ማድረጉ ተገለጸ። ከመስከረም 23 እስከ 25 ቀን 2011 ዓ.ም በሀዋሳ የሚካሄደውን የድርጅቱ 11ኛ መደበኛ ጉባዔ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢህአዴግ) ጽህፈት ቤት ኃላፊ መግለጫ ሰጥተዋል። በዚህ ወቅትም የኢትዮጵያ ለውጥ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በግልጽ ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች መሰረት የመጡ መሆናቸውን ህብረተሰቡ ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል ኃላፊዋ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር። በድርጅቱና በሊቀ-መንበሩ መካከል ልዩነት እንዳለ አድርጎ ማሰብ ተገቢ አይደለም ያሉት ኃላፊዋ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በአገሪቷ እየታዩ ያሉ ለውጦች ሊመጡ የቻሉት ድርጅቱ ገምግሞ ባስቀመጣቸው ግልጽ አቅጣጫዎች ነው ሲሉም ተናግረዋል። ባለፉት አምስት ወራት በአገሪቱ የመጡ ለውጦች መገምገማቸውን ተናግረው የተጀመሩ መልካም ጅምሮች ቢኖሩም ህብረተሰቡ ከሚፈልገው አኳያ ስራዎቹ ገና ጅምር ናቸው ብለዋል። ከዚህም ሌላ ባለፉት አምስት ወራት በአገሪቱ ስርዓተ-አልበኝነት በስፋት እየተስተዋለ መሆኑ ተገምግሟል ያሉት ኃላፊዋ ህብረተሰቡ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ህገ-መንግስታዊ መብቱን ማረጋገጥና ብሄር ተኮር የሆኑ ጥቃቶችን መከላከል ላይ ክፍተት መኖሩን አስታውቀዋል። በሰው ህይወትና በንብረት ላይ እየደረሱ ያሉ ጉዳቶችን ለማስቆም መንግስት ጠንካራ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት በኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴና በምክር ቤቱ መገምገሙንም አስታውቀዋል። በድርጅቱ 11ኛ መደበኛ ጉባኤ ህዝቡ ትክክለኛ "የመደመር" እሳቤ የሚይዝበት አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ነው ወይዘሮ ፈትለወርቅ የተናገሩት። ሁሉም ብሄራዊ ድርጅቶች በየራሳቸው መንገድ ችግራቸውን ለማስወገድና ለውጡን ለማስቀጠል ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውና በብሄራዊ ድርጅቶች መካከል ልዩነት እንደተፈጠረ ተደርጎ የሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል። ከመስከረም እስከ መጋቢት 2010 ዓም በነበሩ የግምገማ መድረኮች እያንዳንዱ ብሄራዊ ድርጅት እየተገመገመ መምጣቱንም አስታውቀዋል። 11ኛው የኢህአዴግ መደበኛ ጉባዔ ''በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ የለውጥ እንቅስቃሴውን በማስቀጠል የኢትዮጵያ ህዳሴን እናረጋግጥ" በሚል መሪ ሀሳብ ነው የሚካሄደው።