ቀጥታ፡

በውጭ አገራት ለስራ የሚሰማሩ ዜጎች የሰለጠኑና ብቁ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው-የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር

ነሐሴ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ)በውጭ አገራት ለስራ የሚሰማሩ ዜጎች የሰለጠኑና ብቁ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ።

በውጭ አገራት ለስራ የሚሰማሩ ዜጎች መብታቸው ተከብሮ እንዲሰሩ መንግስት ልዩ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን፤ ለዜጎች በአገሪቷ የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ በውጭ አገራትም በህጋዊ መንገድ የስራ ስምሪት በማድረግ የስራ እድሎች እየተመቻቹ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በውጭ አገራት የሚሰማሩ ዜጎች ብቁ እና ተወዳዳሪ ሆነው እንዲሰሩ ለማድረግ የስራ ስምሪቱ በሕግ ማአቀፍ እንዲደገፍ መደረጉን ተናግረዋል።

ለዚህም ሲባል በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዘመናዊ አሰራርን ተከትሎ የሰው ኃይል ልማት ላይ የሚሳተፍ ክፍል መደራጀቱን ገልጸዋል።

የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት ረገድ ከበርካታ ሀገራት ጋር ጅምር ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመው ከኩዌት ጋር የሁለትዮሽ የጋራ ስምምነት መደረሱን እና ወደ ተግባር እየተገባ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከኩዌት ጋር ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ ለርካታ ዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጠር ይሆናል ብለዋል።

ከባህሬንና ከሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ጋርም እንዲሁ በሕጋዊ መንገድ የስራ ስምሪት እንዲኖር ጅምር ስራዎች ስለመኖራቸው አቶ ንጉሱ ጠቁመዋል።

ከተባበሩት አረብ ኤምሬትና ኳታር ጋር በተደረገው ስምምነት መሰረት ነርሶችን ወደ ስፍራው መላክ ተችሏል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ወደ መካከላኛው ምስራቅ፣አውሮፓ እና ወደ ሌሎች የዓለም ሀገራት ተንቀሳቅሶ የሚሰራ ብቁ የሰው ሃይል ማፍራት መቻሏ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋትም አንስተዋል።

የቤት ውስጥ ሠራተኞችን በከፊል እና ሙሉ በሙሉ በማሰልጠን ወደ መካከለኛው ምስራቅ፣አውሮፓና ሌሎች ሀገራት ለመላክ ተቋማዊ አደረጃጀቱ እንዲሻሻል እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

በተጨማሪም ስራውን የሚመራ ክፍል መደራጀቱን ጠቁመው ገበያውን የማጥናት፤ የሰው ሃይል አቅምን የመገንባት ስራም እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

ዜጎች መብታቸው፣ደህንነታቸው እና ክብራቸው ተጠብቆ በችሎታና አቅማቸው ሠርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ከተለያዩ ሀገራት ጋር ስምምነት የማድረግ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም