በአማራ ክልል በገጠር የስራ እድል ፈጠራ ከ 500 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በገጠር የስራ እድል ፈጠራ ከ 500 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል ተፈጥሯል
ባህር ዳር ነሀሴ 11/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በገጠር የስራ እድል ፈጠራ ከ511 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው የገጠር ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቡድን መሪ አቶ በለጠ ገበየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በመጀመሪያው ግማሽ በጀት አመቱ በነበረው የህልውና ዘመቻ የገጠር የስራ እድል ፈጠራ ማከናወን እንዳልተቻለ አስታውሰዋል።
ካለፈው ጥር ወር /2014 ጀምሮ ለገጠር ስራ እድል ፈጠራ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ ከእቅድ በላይ ማከናወን እንደተቻለ ተናግረዋል።
በበጀት አመቱ በገጠር የስራ እድል ፈጠራ ለ454 ሽህ 605 የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ በተሰራው ስራ ከእቅድ በላይ ለ511 ሽህ 127 ሰዎች የስራ እድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
በተደረገው የተቀናጀ ርብርብ የእቅዱን 112 በመቶ ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።
የስራ እድሉ ከተፈጠረባቸው መስኮች መካከል ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ አገልግሎት፣ንግድ ዘርፎች መሆናቸውንም ቡድን መሪው አብራርተዋል።
ካለፈው ልምድ በመቀመርም በአዲሱ በጀት ዓመት ለ618 ሽህ 96 ሰዎች የገጠር የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ የልየታ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አቶ በለጠ አስታውቀዋል።
በበጀት ዓመቱ በገጠር የስራ እድል ከሚፈጠርላቸው መካከል 49 ሽህ የሚሆነው ከከፍትኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ስራ ፈላጊዎች መሆኑን ገልፀዋል።
በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ዘንዘልማ ቀበሌ በአትክልትና ፍራፍሬ ችግኝ ማፍላት ስራ የተሰማሩት የካሣሁን ወንዴና ጓደኞቹ ማህበር ስራ አስኪያጅ ወጣት ካሣሁን እማኛው እንዳለው መንግስት በገጠር የስራ እድል በመፍጠር ድጋፍና ክትትል እያደረገ ነው።
ሦስት ሆነው በመደራጀት በተፈጠረላቸው የስራ እድል በዚህ የክረምት ወቅት ብቻ ካፈሉት 70 ሺህ ችግኝ እስካሁን ከ20 ሽህ በላይ የሚሆነውን የማንጎና የአሾካዶ ችግኞች በመሸጥ ከ500 ሽህ ብር በላይ ገቢ ማግኘት እንደቻሉ ተናግሯል።
በየደረጃው ያለ የሚመለከተው የመንግሰት አካል አስፈላጊውን የክህሎት ስልጠናና የገበያ ተደራሽነትን የማስፋት ስራ እንዳመቻቸለቻው ጠቅሷል።
በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ965 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።