የአገር ውስጥ የመድሃኒት አምራችና አቅራቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች አቅርቦታቸው ቀንሷል-የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
የአገር ውስጥ የመድሃኒት አምራችና አቅራቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች አቅርቦታቸው ቀንሷል-የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት

የአገር ውስጥ የመድሃኒት አምራችና አቅራቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች አቅርቦታቸው መቀነሱን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ገለጸ።
አገልግሎቱ በቀጣይ ምርትና አቅርቦታቸውን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን እንደሚያከናውን አስታውቋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ያሉትን ችግሮች በመፍታት የአገር ውስጥ መድኃኒት አቅራቢዎችና አምራቾችን አቅም ለማሳደግ በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ከአገር ውስጥ መድኃኒት አቅራቢዎችና አምራቾች ጋር በሕክምና ግብዓቶች አቅርቦት አፈጻጸም ላይ ውይይት አካሂዷል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ እንዳሉት በኮሮናቫይረስ፣ በአገሪቱ በተከሰተው የጸጥታ ችግር፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረትና በባለሀብቶቹ የአቅም ውስንነት አቅርቦቱ ቀንሷል።
በዚህም በ2015 በጀት ዓመት ያሉትን ችግሮች በመፍታት የአገር ውስጥ አቅራቢዎችና አምራቾችን አቅም ለማሳደግ በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።
የአገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾችና አቅራቢዎች ምርታማነትና አቅርቦት ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ እየቀነሰ መምጣቱን ጠቁመዋል።
የአገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾችን አቅራቢዎችን የምርት አቅም ወደ 60 በመቶ ለማሳደግ ቢሰራም ግቡን ማሳካት እንዳልቻለ ጠቁመዋል።
ለአብነት የአገር ውስጥ አምራቾችና አቅራቢዎች የገበያ ሽፋን በ2010 ዓ.ም 25 በመቶ እንደነበር አስታውሰው በ2014 ዓ.ም በእጅጉ በመቀነስ ወደ 8 በመቶ ማሽቆልቆሉን ገልጸዋል።
በ2014 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ መድኃኒት ለማቅረብ ቀጥታ ግዥ ተፈቅዶላቸው ውል ከገቡት መካከል በዓመቱ መጨረሻ 10 በመቶ አፈጻጸም ያሳዩ ተቋማት መኖራቸውን ተናግረዋል።
የአገር ውስጥ አምራቾቹን ዝቅተኛ አፈጻጸም ለማሻሻል በመሰረታዊነት የግብዓት አቅርቦቱን ለማሳደግ ሰፊ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በዚህም የባለድርሻ አካላት የተጠናከረ የጋራ ስራ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ለ5 ሺህ ጤና ጣቢያዎች 60 በመቶ የሕክምና ግብዓቶችን ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዘርፉ የተሰማሩት ባለሀብቶች በበኩላቸው ያሉትን ችግሮች በመፍታት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን በጋረ መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
በዚህም የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ፣የኃይል መቆራረጥ ፣በጉምሩክ ላይ ያለው ቢሮክራሲ እና ከቁጥጥር ባለስልጣን ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል።