በአዲስ አበባ ከተማና ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን መካለል ለዘመናት ለቆየዉ ማነቆ ዘላቂ መፍትሔ ነዉ!

147

በአዲስ አበባ ከተማና ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል ግልፅ የሆነ የአስተዳደር ወሰን ሳይካለል ቆይቷል፡፡

በየትኛዉም እርከን ባለዉ አስተዳደራዊ አደረጃጀት መካከል ወሰን አስፈላጊ ቢሆንም በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል አስተዳደርዊ ወሰን ባለመካለሉ ምክንያት በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ እንግልትና በደል ሲደርስበት ቆይቷል፡፡

ለአብነትም በአዋሳኝ አካባቢ የሚኖሩ የልዩ ዞኑም ሆነ የአዲስ አባባ ነዋሪዎች የሚገባቸውን የመንግስት አገልግሎት ለማግኘት አልቻሉም፡፡

የመሰረተ ልማት ዝርጋታና ለህዝቡ ወሳኝ የሆኑ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመስራት ከፍተኛ መስተጓጎልና መጓተት ብሎም መቋረጥ አጋጥሟል።

በአዲስ አባባ አፍንጫ ስር ሆነዉ የልዩ ዞኑ ነዋሪ ልጆች የአንደኛና ሁለተኛ ትምህርት ቤትን ለመፈለግ 40 እና 50 ኪሎሜትር ርቆ ለመሄድ ተገዷል፡፡

ሌሎች መንግስታዊ አገልግሎት ለማግኘትም እንደዚሁ፡፡ ከሁሉም በላይ የመሬት ወረራን ጨምሮ ሌሎች ህገ ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር፤ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና ተጠያቂነትን ለማስፈን አዳጋች ሆኖ ቆይቷል፤ ነዋሪዎች ያለ አግባብ ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዋል፤ ቤተሰብ ተበትኗል፤ ለኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ቀዉስ ተዳርጓል፡፡

ከዚህም አልፎ ችግሩ ለፖለቲካ ቀዉስም ዳርጎናል፡፡ ከተማ አስተዳደሩና ልዩ ዞኑ ተቀናጅተውና ተደጋግፈው በጋራ እንዳያድጉና እንዳይለሙ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል።

በአስተዳደር ወሰን አለመካለል ምክንያት አሁንም ድረስ በሁለቱም በኩል ህዝቡ በወሳኝ አገልግሎት እጦት፣ ተገቢዉ መሰረተልማት ባለመዘርጋትና በሕገ ወጥ ተግባራት መንሰራፋት ምክንያት ሕዝቡ ለችግር ተጋልጧል፡፡

በአካባቢዎቹም ተደጋገም ግጭቶችና የደህንነት ስጋቶች አጋጥማዋል፡፡በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል መኖር የሚገባዉ አስተዳደራዊ ወሰን ባለመኖሩ የሕዝብ ጥያቄም ሆኖ ቆይቷል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በተለያዩ ጊዜያት ልዩ ዞኑና ከተማ አስተዳደሩ በተናጠልና በጋራ ጥናቶቹን በማካሄድና ኮሚቴዎችን በማዋቀር ያደረጉት ሙከራዎች መፍትሔ ማምጣት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

ይህ በመሆኑም በሁለቱም አካባቢዎች በሚኖረዉ ሕብረተሰብ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ስለሆነም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአስተዳደር ወሰን ጉዳዩን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል ከከተማ አስተዳደሩና ከልዩ ዞኑ የተውጣጣ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሰፋ ያለ ጥናት በማድረግ የአስተዳደር ወሰን የማካለል ሥራዉ የፌዴራል መንግስትና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ሕገ-መንግስት እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተርን መሰረት በማድረግ የሁለቱን አከባቢዎች የጋራ ተጠቀሚነትና ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ በሚያስችል ሆኔታ የማካለሉ ተከናዉኗል፡፡

በሁለቱም አስተዳደር አመራር አካላት መካከልም ሰፊ ዉይይት ከተደረገ በኋላ በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር መካከል ስምምነት ተፈጽሟል፡፡ የሁለቱም አካባቢ ነዋሪዎችም በጉዳዩ ላይ ተወያይተው ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

ሥራዉ በሚከናወንበት ወቅት የፌዴራል መንግስትም የቅርብ ክትትል በማድረግ ጉዳዩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ሰርቷል፡፡ በዚህ መሰረት የአስተዳድር ወሰኑ ሲካለል የከተማ አስተዳደሩንና የልዩ ዞኑን ህዝቦች በጋራ አብሮ መልማትን፣ መሰረት ያደረገ፤ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር እንዲያጠናክር ታሳቢ ያደረገ፣ የአስተዳደር ወሰን ጉዳዩ ወቅታዊ ሳይሆን ዘላቂና የረጅም ጊዜ መፍትሄ እንዲሆንና ለዘመናት ይደርስ የነበረውን በደልና ጉዳት በሚያስወግድ መልኩ ተጠናቋል፡፡

በመሆኑም የአስተዳደር ወሰኑ መሬት ላይ ወርዶ በሁለቱም በኩል መደበኛ ስራ እስኪጀመር ቀድሞ የነበረዉ መደበኛ የአገልግሎት አሰጣጡና የፀጥታ ማስከበር ስራዎች ሳይስተጓጓሉ ይቀጥላሉ፡፡

የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችም በተያዘዉ መንገድ የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡ የመሰረተ ልማት ዝርጋታም ሳይስተጓጎል ይቀጥላል፡፡ ዉሳኔዉ ሕገ-ወጥነትን ለመከላከል፣ የሕግ የበላይነትን በጋራ ለማስፈን እንዲሁም ለጋራ ልማትና እድገት ዘላቂ መፍትሔ በመሆኑ ሁሉም አካላት ለተግባራዊነቱ እንዲተባበሩ መንግስት ጥሪዉን ያስተላልፋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል የተደረገዉ የአስተዳደር ወሰን የማካለል ሥራ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የወሰን ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በዘላቂነት ለመፍታት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አካል ሲሆን በሁለቱም ወገኖች መካከል የተደረገዉ የአስተዳድር ወሰን ማካለል ሥራ የነበረዉን ማነቆ በዘላቂነት የሚፈታና በሌሎች አካባቢዎችም ለሚነሱ ተመሳሳይ ጉዳዮች ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ሥራ ነዉ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም