በሲዳማና ኦሮሚያ ክልሎች በአጎራባች ወረዳዎች ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በተሰራው ቅንጅታዊ ስራ ውጤት ተገኝቷል

53

ነሐሴ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሲዳማና ኦሮሚያ ክልሎች አጎራባች ወረዳዎች ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በተከናወነው ቅንጅታዊ ስራ ውጤት መገኘቱን ክልሎቹ ገለጹ።

በ2014 በተከናወኑ የሰላምና ጸጥታ ተግባራት ላይ ያተኮረ ውይይት የሁለቱ አዋሳኝ ከሆኑ 17 ወረዳዎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ዛሬ በሀዋሳ ከተማ መክረዋል።

የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ እንደገለጹት በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ ህዝቦች ለዘመናት ተዋደው፣ተከባብረውና ተዋልደው የኖሩ ናቸው።

አልፎ አልፎ የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በማባባስ ወደ ግጭትና ብጥብጥ እንዲገቡ በሚያደርጉ ሸኔና ሌሎች በሽብር የተፈረጁ ቡድኖች ሴራ አካባቢውን የግጭት ቀጠና ለማድረግ ተሞክሯል ነው ያሉት።

ክልሎቹ በሚዋሰኑባቸው ወረዳዎች ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በአመራሩና በህዝቡ መካከል የተፈጠረው ቅንጅታዊ ስራ ውጤት እያመጣ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ህብረተሰቡን ያማካለ የሰላምና የጸጥታ ስራ መሰራቱ ለተገኘው አመርቂ ውጤት የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል።

እንደ አቶ አለማየሁ ገለጻ በአካባቢው የመጣው ሰላም በአባገዳዎችና በሲዳማ ሽማግሌዎች ጥረት መሆኑን ገልጸው ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ክልል መዋቅር የተወሰደው የአመራር ቁርጠኝነት ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግና የህብረተሰቡን ትስስር ለማጠናከር በበጀት ዓመቱ የተገኙ ተሞክሮዎችን ማስፋትና በውጤቱ የተሳተፉ አካላትን ማመስገን ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

የቢሮው ምክትልና የግጭት አፈታት ዘርፍ ሃላፊው አቶ አለማየሁ አሰፋ በበኩላቸው በአዋሳኝ አካባቢዎቹ በግጦሸ መሬት፣ በወሰን፣ በእንስሳት ስርቆት በመሳሰሉ ጥቃቅን ጉዳዮች አለመግባባቶች እንደሚፈጠሩ ተናግረዋል።

ችግሩን በዘላቂነት መፍታት እንዲቻል የሁለቱ ክልሎች አመራሮች የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ መቻሉን ተናግረዋል።

"በ2014 የነበረው አፈጻጸም የተሻለ መሆኑን ገልጸው አለመግባባቶችን የብሄር ግጭት በማስመሰል ለማባባስ ከመሞከር ይልቅ አጥፊን በህግ ተጠያቂ በማድረግ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ልምድ እየዳበረ መጥቷል" ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ በስድስት ወረዳዎች ላይ የተከሰቱ ጥቃቅን አለመግባባቶችን ለመፍታት የተከናወኑ ተግባራት ለሌሎች አካባቢዎችም ጭምር ተሞክሮ እንዲሆኑ ውይይት እንደተደረገበት ተገልጿል።

ሁለቱ ህዝቦች የጋራ የሆነ ባህላዊ እሴት ያላቸው በመሆኑ አለመግባባቶችን በባህላዊ የእርቅ ስነስርዓት ለመፍታት የሚያስችሉ ህዝባዊ መድረኮች መከናወናቸውንም ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል የምእራብ አርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሃጂ በበኩላቸው የሁለቱን ህዝቦች ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ ትስስሮችን ለማጠናከር የአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅ ቀዳሚ ስራ መሆኑን ተናግረዋል።

በ2014 በአመራሩ በተወሰደው አቋም ውጤት እንደተመዘገበ ገልጸው ቀጣይነት እንዲኖረው ቅንጅታዊ ስራውን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።

ግጭት በሚፈጠርበት አካባቢ ከቀበሌ ጀምሮ ያለ አመራር ተጠያቂ የሚሆንበት አሰራር ተግባራዊ መደረጉን ገልጸው በአዲሱ በጀትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።

የሁለቱ ክልል አመራሮች መቀናጀት፣የህዝቡን ባህልና ወግ የተከተለ የአባገዳዎችና ሽማግሌዎች ጥረትና የመንግስት የህግ ማስከበር ዘመቻ ውጤታማ መሆኑንም የገለጹት ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በሲዳማ ክልል የብላቴ ዙሪያ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ቶማስ አናቶ ናቸው።

በቀጣይ ከሚያጋጩን ይልቅ አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ በመስራት ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እንተጋለን ብለዋል።

የተገኘው ስኬት እንዲቀጥል የአመራሩ ሚና ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ከምእራብ አርሲ ዞን የኮኮሳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አሊ ጋለቶ ናቸው።

ከሲዳማ ከሚዋሰኑባቸው ወረዳዎች ጋር ተቀናጅተው በመስራት ወንጀለኞችን የማጋለጥና በህግ የማስጠየቅ ስራው በትኩረት የተከናወነበት ዓመት እንደሆነ ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል መልጋ ወረዳ የሃገር ሽማግሌ አቶ ዱጉኖ ታሚሶ የሽምግልና ልምዳቸውን ተጠቅመው በአካባቢው ሰላም ለማምጣት መስራታቸውን ተናግረዋል።
ሰላም የልማት ሁሉ መሰረት በመሆኑ ከኦሮሞ አባገዳዎች ጋር ተባብረን ለሰላም መጠናከር እሰራለን ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የአካባቢው ሰላም በማስጠበቅ ሂደት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት ምስጋናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም