በዞኑ ከ1 ሚሊየን በላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኝ ተከላ ተከናውኗል--መምሪያው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ከ1 ሚሊየን በላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኝ ተከላ ተከናውኗል--መምሪያው

ደብረ ማርቆስ ነሐሴ 10/2014 (ኢዜአ) በምስራቅ ጎጃም ዞን በተያዘው ክረምት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ የፍራፍሬ ችግኝ መተከሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የመስኖ ልማት ቡድን መሪ አቶ ሀብታሙ አህመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት አርሶ አደሩ ከሰብል ልማቱ ጎን ለጎን በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በመሳተፍ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
በተያዘው የክረምት ወቅት ለተከላ የሚውሉ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ የቡና፣ የአቮካዶ፣ የማንጎ፣ የብርቱካን፣ የሎሚ እና የአፕል ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ነው የጠቀሱት።
በተደረገው ጥረት ከ1 ሚሊየን 290 ሺህ በላይ የቆላና የደጋ የፍራፍሬ ችግኞችን መተከሉን ገልጸው
በተከላውም ከ1 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መሸፈኑን ተናግረዋል።
ከ30 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ገልጸው በሦስት ወረዳዎች በኩታ ገጠም በ130 ሄክታር መሬት ላይ 195 ሺህ ችግኝ መልማቱን ገልጸዋል።
በበጀት አመቱ የተተከለው የፍራፍሬ ችግኝ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ200 ሺህ ችግኝ ጭማሬ እንዳለው አብራርተዋል።
አርሶ አደሩ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተጠቃሚ እየሆነ በመምጣቱ በዘርፉ የመሰማራት ፍላጎት መጨመር ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
የስናን ወረዳ የረቡ ገቢያ ከተማ ነዋሪ አርሶ አደር ላቃቸው ያዜ በሰጡት አስተያየት በዚህ ክረምት 100 የአፕል ችግኝ መትከላቸውን ተናግረዋል።
የተከሉት ችግኝ ፀድቆ ለውጤት እንዲበቃም ተገቢውን እንክብካቤና ጥበቃ እንደሚያደርጉ ጠቅሰዋል።
ከአምስት አመት በፊት 50 የአፕል ችግኞችን በጓሯቸው በመትከል አሁን ላይ ለገበያ በማቅረብ በሚያገኙት ገቢ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዘንድሮው አመት ሩብ ሄክታር ማሳ ላይ የቡና ችግኝ መትከላቸውን የተናገሩት ደግሞ የማቻከል ወረዳ አርሶ አደር ምህረት ይኽነው ናቸው።
የፍራፍሬል ልማት ጠቀሜታው የጎላ ቢሆንም የቦታ እጥረት ማነቆ እንደሆነባቸውም ገልፀዋል።
ከ6 አመት በፊት በሩብ ሄክታር ማሳ ላይ ከተከሉት የቡና ምርት ሽያጭ በዓመት ከ40 እስከ 50 ሺህ ብር ገቢ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ባለፉት ሰባት ዓመታት በተደረገ የአትክልትና ፍርፍሬ ልማት ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መሸፈን እንደተቻለ ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።