በተዛባ የታሪክ አረዳድ ወደ ግጭት የሚመሩ አካላትን ፍላጎት በማስረጃ ማክሸፍ ይገባል - ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ

224

ነሐሴ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በተዛባ የታሪክ አረዳድ ልዩነት በመፍጠር ማኅበረሰቡን ወደ ግጭት የሚመሩ አካላትን ፍላጎት በማስረጃ ላይ ተመስርቶ ማክሸፍ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበርና በፍሬድሪክ ኤበርት ፋውንዴሽን ትብብር የተዘጋጀ አውደ-ጥናት "ትስስርና መስተጋብር በኢትዮጵያ ታሪክ" በሚል መሪ ሀሳብ ተካሂዷል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ፤ ታሪክ የአንድ ነገር የመሆን እና አለመሆን እውነትነትን ከመግለጽ ባለፈ የታሪክ ጸሐፊዎች ለራሳቸው ፍላጎት ያጋደለ እይታቸውን የሚያሰፍሩበት መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት በዜጎች መካከል ልዩነትና መቃቃር ለመፍጠር የሚፈልጉ ኃይሎች ትልቁ የማደናገሪያ መሳሪያቸው ሆኖ እንደሚያገለግል ተናግረዋል።

በመሆኑም ታሪክን በማዛባት በማኅበረሰቡ ዘንድ ግጭት ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላትን በእውነተኛ ማስረጃ በመሞገት ፍላጎታቸውን ማክሸፍ ይገባል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲፈጠር የታሪክ ምሁራን የጎበጠውን የታሪክ አረዳድ በማቃናት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

ኢምሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ረዥምና ደማቅ ታሪክ ያላት አገር ብትሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታሪክ የፖለቲካ ግብግብ አውድማ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

በዚህም በተለያዩ አካባቢዎች አለመግባባቶችና ግጭቶች መፈጠራቸውን ገልጸው፤ በ1983 ዓ.ም የተደረገው የሥርዓት ለውጥ መፈክሩ "ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት" ወይም "አንድነት በብዝሀነት" ቢሆንም አንድነቱ ሳይሆን ብዝሀነቱ ገኖ ወጥቷል ብለዋል።

በመሆኑም ከልዩነት ይልቅ ለአንድነት ቅድሚያ አጽንኦት በመስጠት ሕብረ-ብሔራዊ የሆነው ታሪካችን ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር የሚችልበት እድል ጎልቶ መውጣት አለበት ብለዋል፡፡

በመድረኩ ተሳታፊ የነበሩት ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እና ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ፤ በታሪክና ትርክት መካከል ያለው ልዩነት ተነጥሎ መውጣት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

የታሪክ ምሁራን ሀቅን በማውጣት የኢትዮጵያዊያን የሆኑ የጋራ ባህሎችና መስተጋብሮችን አጉልተው ማሳየት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም