የአሜሪካ አለም አቀፍ እርዳታ ድርጅት ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር የ7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር የስልጠና ስምምነት ተፈራረሙ

71

ነሐሴ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ)የአሜሪካ አለም አቀፍ እርዳታ ድርጅት /ዩ ኤስ ኤይድ/ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር የ7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር የስልጠና ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱ በአደጋ መከላከልና ምግብ ጥናት መስክ ብቁና ተወዳዳሪ ተመራማሪዎችንና አመራሮችን ለማፍራት ያለመና ለአምስት ተከታታይ ዓመታት የሚቆይ መሆኑ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የዩ ኤስ ኤይድ ዳይሬክተር ሾን ጆንስ በስምምነት ስነ-ስርአቱ ወቅት እንዳሉት የተደረገው ስምምነት የኢትዮጵያን የአደጋ ተጋላጭነት ለመቀነስ ያለመ ነው።

ባለፉት 10 ዓመታት በአደጋ መከላከልና ተጋላጭነት ቅነሳ ዘርፍ የሚካሄደውን የትምህርት ፕሮግራም በመደገፍ መስራታቸውን ገልፀዋል።

May be an image of 3 people and people standing

በዛሬው ስምምነት መሰረትም 750 ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን በአደጋ መከላከልና ምግብ ጥናት የትምህርት ዘርፍ ለማሰልጠን ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም በቀጣዩ ትውልድ ላይ በአደጋ መከላከልና ተጋላጭነት ቅነሳ ዙሪያ ተከታታይነት ያለው አቅም ግንባታ በመስራት በዘርፉ ብቁ አመራር ለመፍጠር እንደሚያስችል አስረድተዋል።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽንና ስትራተጅክ ኮምዩኒኬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ዘውዱ እምሩ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከ400 በላይ የትምህርት ፕሮግራሞችን ከፍቶ የተማረ የሰው በሀይል እያፈራ ይገኛል።

ፕሮግራሞቹ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚፈልገውንና በአደጋ መከላከልና ተጋላጭነት ቅነሳ ላይ የሚያስፈልገውን የሰለጠነ የሰው ሃይል በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ዩ ኤስ ኤይድ በዩኒቨርሲቲው አዳዲስና ጠቃሚ የትምህርት ክፍሎችን ከፍቶ እንዲሰራ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።

የዛሬው ስምምነትም አደጋ መከላከልና ምግብ ጥናት ጋር በተያያዘ ብቁ ተመራማሪዎችና አመራሮችን ለማፍራት ያለመ ሲሆን ከ11 ዩኒቨርስቲዎች የሚመጡ ምሁራን ይሳተፋሉ ብለዋል።

የዩ ኤስ ኤይድ ልኡካን ቡድን ከባህር ዳር ከተማዋ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ጋር በሰላምና ልማት ላይ ያተኮረ ውይይትም አካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም