በምርምር ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ 13 ቴክኖሎጅዎችን ለማስፋት ስምምነት ላይ ተደረሰ

110

ባህር ዳር፤ ነሐሴ 9/2014 (ኢዜአ)፡ በአማራ ክልል በዘላቂ መሬት አስተዳደር ላይ በተካሄደ ምርምር ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ 13 ቴክኖሎጅዎችን ለማስፋት የሚያስችል ስምምነት መደረሱ ተገለጸ።

''ቶቶሪ'' እና ''ሽማኔ'' የተባሉ የጃፓን ዩኒቨርሲቲዎች ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለአምስት ዓመታት ያካሄዱትን የምርምር ውጤት ለመተግበር የሚያስችል ስምምነት ዛሬ አድርገዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር አልማዝ ጊዜው በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት የክልሉ ስነ- ምህዳር ለአፈር መከላት የተጋለጠ ነው።

ችግሩን ለመቅረፍ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ ከማከናወን ባለፈ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተካላ ተግባር  እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የሚከናወኑ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራዎች በሳይንሳዊ ምርምሮችና ቴክኖሎች ባለመታገዛቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩን መፍታት አለመቻሉን አስረድተዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከጃፓን ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ሲያካሂድ የቆየው የምርምር ስራ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራን፣ የመሬት ለምነት፣ ምርታማነትንና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በማቀናጀት ለውጥ ያመጣ ነው ብለዋል።

የምርምር ግኝቱን በማስፋት የህብረተሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማሳዳግም ቢሮው ከምርምር ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ ለመስራት ዛሬ ስምምነት ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በበኩላቸው ምሁራኑ በየሙያ ዘርፋቸው ችግር ፈች የምርምር ስራዎች ላይ በማተኮር እየሰሩ መሆኑን ገለጸዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከጃፓን ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ሲያካሂድ የቆየው የምርምር ስራ በአይነቱ ልዩ መሆኑን ተናግረዋል።

 የምርምር ግኝቱን ወደ ሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በማስፋት ህብረተሰቡን በዘላቂነት ተጠቃሚ ለማድረግ በሚደረገው ጥረትም ዩኒቨርሲቲው የድርሻውን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።

 የምርምር ስራው በ3 ሚሊየን ዶላር በጀት ለአምስት ዓመታት የተካሄደ መሆኑን ያስረዱት ደግሞ በጃፓን ቶቶሪ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ፕሮፌሰር ንጉሴ ሐረገወይን ናቸው።

ምርምሩ የዘርፉን ምሁራን ባሳተፈ መልኩ  በተጨባጭ ችግሮች ላይ ትኩረት በማድረግ ውጤታማነታቸው በተረጋገጡ  13  ፕሮጀክቶች ላይ መካሄዱን አመልክተዋል።

የምርምሩ አላማ  የአፈርና ውሃ መከላትን መቀነስ፣ የአፈር ለምነትን ማሳደግ፣ ምርታማነትን መጨመርና የአካባቢውን ማሀብረሰብ ዘላቂ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አቀናጅቶ በመተግበር ለውጥ ማምጣት መሆኑን ገልጸዋል።

በአባ ገሪማ፣ ጉደርና ድባጤ አካባቢዎች በተካሄደው የሙከራ ትግበራ የአፈር መከላትን እስከ 96 በመቶ መቀነስ ሲቻል የመሬቱን ምርታማነት በ130 በመቶ ማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በፕሮጀክቱ የታቀፉ የማህበረሰብ ክፍሎች ገቢን በ35 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰው፤ ፕሮጀክቱን ለማስፋት የሚያስችሉ ሁለት የጥናት ሰነዶች  መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።

ፕሮጀክቱ 12 ተማሪዎችን በ3ኛ ዲግሪ በጃፓን ዩኒቨርስቲዎች  በማስተማርና በ12 ሚሊየን ብር ወጭ ለምርምር የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን በማስገባት ጥቅም ላይ ማዋል መቻሉን አስረድተዋል።

ፕሮጀክቱ እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ድርጅታቸው የሃብት ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን የተናገሩት ደግሞ በጃይካ የኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት ዋና ተጠሪ ሚስተር ካትሱኪ ሞሪሃራ ናቸው።

ቴክኖሎጅዎቹ በሙከራ ትግበራ ውጤታማነታቸው መረጋገጡን ያስረዱት ሚስተር ካትሱኪ፤ በቀጣይ ቴክኖሎጅዎችን  ለማስፋት የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።    

ፕሮጀክቱን ወደ ታች በማውረድ ወደ ሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለማስፋት  የክልሉ ግብርና ቢሮ፣ የክልሉ ግብርና ምርምር፣ የባህርዳር ዩኒቨርስቲና ሁለቱ የጃፓን  ዩኒቨርሲቲዎች የጋራ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም