ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተፋሰሱ አገራት ምንም አይነት ጉዳት እንደማያደርስ አረጋግጠናል - የደቡብ ሱዳን ልዑክ

106

ነሐሴ 09 ቀን 2014( ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተፋሰሱ አገራት ምንም አይነት ጉዳት እንደማያደርስ አረጋግጠናል ሲሉ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች አማካሪ ኮንግ ቲፕቲፕ ጋትሏክ ገለጹ፡፡

የመከላከያ ሚኒስትርና የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አብርሃም በላይ፤ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያንም የጋራ የልማት ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት እያደረገ የሚገኘው የደቡብ ሱዳን የደኅንነትና ሲቪል ሹማምንት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል።

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች አማካሪ ኮንግ ቲፕቲፕ ጋትሏክ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለተፋሰሱ አገራት ጭምር የልማት ፕሮጀክት ነው፡፡

ከኢትዮጵያ መንግሥት በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ለጉብኝት መምጣታቸውን የገለጹት የፕሬዝዳንቱ የደኅንነት ከፍተኛ አማካሪ፤ በጉብኝታቸውም የሕዳሴ ግድብ ጎረቤት አገራትን በኃይል የሚያስተሳስር ፕሮጀክት መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮች በድርድር መፈታት እንዳለባቸው ገልጸው፤ ባደረግነው ጉብኝትም ግድቡ የጋራ የልማት ፕሮጀክት እንጂ ምንም አይነት ችግር የለውም ብለዋል።

የኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስትርና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አብርሃም በላይ፤ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካዊያን በተለይም ለጎረቤት አገራት የጋራ የልማት ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ፣ ለሱዳንና ጂቡቲ  ኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ጀምራለች፤ ለኬንያ በቅርቡ መላክ እንጀምራለን፤ ደቡብ ሱዳንም የኃይል እጥረት ስላለባት ፍላጎት አላት እንሰጣለን ብለዋል፡፡

በመሆኑም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያዊያን ብርቱ መስዋዕትነት እየተገባደደ ያለ ፕሮጀክት ቢሆንም የተፋሰሱን ሀገራት ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በግድቡ ግንባታ ሂደት የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ታሳቢ በማድረግ ሁለት ዓመቱን ሙሉ ውሃ የሚፈስባቸው ሁለት የውሃ ማስተላለፊያ ሰፋፊ ቱቦዎች እንዲኖሩ አድርገናል ብለዋል፡፡

የታችኛው ተሳሰስ አገራት ወንድሞቻችን የግድቡ ግንባታ በውጭ ሆነው የሚያወሩ በተግባር ያለው የተለያየ በመሆኑ የጋራ የልማት ፕሮጀክታችን እንደሆነ ይረዱናል ብለዋል ዶክተር አብርሃም፡፡

የኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ጠላቶች የሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንዳይሰሩ፣ ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶች እንዳይገቡ እንዲሁም አስፈላጊ ግብዓቶች እንዳይቀርቡ ክልከላ ሲያደርጉ እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ተመስገን ጥሩነህ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ በውስጥ ባንዳዎችና በውጭ ጠላቶች የተለያዩ ጥቃት እንዲደርስበት ሲደገስለት ነበር ብለዋል፡፡

ሕዝቡ ሲፈነዳና ሲተኮስ አላየም እንጂ ሀብታችንን እንዳንጠቀም በተላላኪ ባንዳዎች የሚላኩ ከመፈንዳታቸው በፊት በርካታ ፈንጂዎችን አክሽፈናል፤ ወደፊትም ግድቡን ለመጠበቅ እንቅልፍ አይኖረንም ብለዋል፡፡

የሕዳሴው ግድብ ግንባታ አፍሪካዊያን የራሳቸውን ሀብት በራሳቸው አቅም መጠቀም እንደሚችሉ ያሳየ መሆኑንም ዳይሬክተር ጄነራሉ ገልጸዋል።

የጎረቤት አገራት ኢትዮጵያ የውሃ ማማ መሆኗን በመረዳት በአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ በመትከል ሌሎች ዓባዮችን መፍጠር እንዲችሉ ጥሪ መቅረቡንም ጠቅሰዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ማብሰራቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም