ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአካባቢ ምርጫ የህግ ማዕቀፍና አፈጻጸም ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች አካላት ጋር ምክክር አካሄደ

107

ነሃሴ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአካባቢ ምርጫ የህግ ማዕቀፍና አፈጻጸም ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች አካላት ጋር ምክክር አካሄደ።

ቦርዱ ለአምስተኛ ጊዜ በሚካሄደው የአካባቢ ምርጫ የህግ ማዕቀፍና አፈጻጸም ላይ ያስደረገውን ጥናት አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች አካላት ጋር ዛሬ ተወያይቷል።

ጥናቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌዴራሊዝምና የአስተዳደር ጥናት ማዕከል የተደረገ ሲሆን የአካባቢ ምርጫ አስፈላጊነት ተመላክቶበታል።

ጥናቱን ያቀረቡት ዶክተር ዘመላክ አየለ እና ዶክተር ክርስቶፍ ቫንደር በፌዴሬሽን የሚተዳደሩ የአለም ሀገራት በአካባቢ ምርጫ ላይ ያላቸውን አለም አቀፍ ተሞክሮ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የአካባቢ ምርጫን ለማካሄድ ያለው የህግ ማዕቀፍ በጥናቱ የተመላከተ ሲሆን ክልሎች ህገ-መንግስቱን መሰረት በማድረግ በተለያዩ ጊዜ ምርጫ ማካሄዳቸው በጥናቱ ተነስቷል።

ቀደም ብለው የተደረጉ ምርጫዎች የቀድሞው ገዥ ፓርቲ ወይም ኢህአዴግ የበላይነት የተስተዋለባቸው እንደነበሩ ጥናት አቅራቢዎች አመላክተዋል።

የአካባቢ ምርጫዎችን ለማካሄድ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተለያዩ ክልሎች ቢሮዎችን መክፈትና ከክልል አስተዳደሮች ጋር በቅርበት መሰራት እንዳለበት ምክረ ሃሳብ ቀርቧል።

ምርጫውን ለማካሄድ የህግ ማዕቀፎችና አስቻይ ሁኔታዎች በጥናት መለየታቸው አስፈላጊ መሆኑ ተሳታፊዎቹ ጠቁመዋል።

የአካባቢ ምርጫ ለረዥም ጊዜ ባለመካሄዱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎችን ተሳታፊዎቹ በአብነት አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ፤ ጥናቱ በቦርዱና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ዋና ዋና ጉዳዮችን ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል።

በአካባቢ ምርጫ ዜጎች በተለያየ ሁኔታ በአግባቡ መወከል የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ቦርዱ የማስፈጸም አቅሙን እስከታች በማጠናከር እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የአገራዊ ምክክር ለማድረግ በሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሰው ከምክክሩ ጎን ለጎን ምርጫ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል እንደተደረገው የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ምርጫ የማይካሄድባቸው መሆኑን ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።

በሂደቱ የተመራጮች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ አፈጻጸሙ የተወሳሰበ እንዳይሆን መሰራት ባለበት ጉዳይ ላይ ለተነሳው ጥያቄም ሰብሳቢዋ ምላሽ ሰጥተዋል።

የአካባቢ ምርጫ የብሔረሰብ፣ የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ የሚካሄድበት እንደሆነ በምርጫ ህጉ ተቀምጧል።

በኢትዮጵያ ቀደም ሲል አራት የአካባቢ ምርጫዎች የተካሄዱ ሲሆን የመጨረሻው ከተካሄደ ከዘጠኝ አመት በላይ ማስቆጠሩ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም