ቀጥታ፡

የህዝብን ሰላምና አንድነት የሚያናጉ የጥላቻ ንግግሮች እንዲገቱ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ መስከረም 7/2011 በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ሳቢያ በደረሰው ጉዳት ማዘኑን የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ። መንግስትም የዜጎችን በሰላም የመኖርና በነጻነት የመንቀሳቀስ ህገ-መንግስታዊ መብት እንዲያስከብርና ስርዓት አልበኛ የሆኑ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ጉባኤው ጠይቋል። ጉባኤው ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳለው፤ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ አክቲቪስቶችና የልዩ ልዩ አደረጃጃት ተወካዮች ከወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ጋር በሚያደርጉት ውይይት የህዝብን ሰላምና አንድነት ከሚያናጉ የጥላቻ ንግግሮች እንዲቆጠቡ አሳስቧል። እነዚህ አካላት የአገርን ሰላምና አንድነትን በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ እንዲያተኩሩም ጉባኤው አሳስቧል። ወላጆች ልጆቻቸው ከማንኛውም ክፉ ተግባር እንዲቆጠቡ ይመክሩ ዘንድ የጠየቀው ጉባኤው "ወጣቶችም ስህተትን በስህተት ከማረም ተግባር በመቆጠብና ያላቸውን ጥያቄ በአግባቡና በስርዓት ለመንግስት በማቅረብ የአገሪቱን ገጽታ ከሚጎዱ ተግባራት መቆጠብ አለባቸው" ሲል  አስገንዝቧል። ጉባኤው አክሎም "ባለፉት ተከታታይ ወራት አገሪቱን ወደቀድሞ ክብሯ ለመመለስ የተከናወኑት በጎ ተግባራት ወደኋላ እንዳይመለሱ የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል" ብለዋል። የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ በግጭቱ ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን ላጡ፣ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው መጽናናትን ተመኝቷል። መንግስት የድርጊቱ ተዋናይ የሆኑትን ስርዓት አልበኞች ህጋዊ መስመር እንዲያሲዝና ዜጎች ከቤት ንብረታቸው እንዳይፈናቀሉ ብርቱ ድጋፍ እንዲያደርግም ጉባኤው ጠይቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም