ኢንስቲትዩቱ የ"ስማርት ሲቲ" ፕሮጀክትና የፋይናንስ ተቋማትን መረጃ የሚይዝ ዘመናዊ የዳታ ማዕከል ገንብቷል

94

ነሐሴ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ)በኢትዮጵያ የከተሞች ደህነንት የ"ስማርት ሲቲ" ፕሮጀክትና የፋይናንስ ተቋማትን መረጃ በማደራጀት የሚይዝ ግዙፍ የዳታ ማዕከል መገንባቱን የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በአገራዊ ችግሮች ላይ የምርምር ስራዎችን በማከናወን ከምስለ ምርት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብቷል፡፡

በትምህርት፣ ጤና፣ ትራንስፖርት፣ በፋይናንስና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ለአገራዊ ችግሮች አገራዊ መፍትሔ ለመሻት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ እያዋለ ይገኛል።

የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታዬ ግርማ፤ ለኢዜአ እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ የተቋቋመበትን አላማ ዕውን ለማድረግ በህግ ከተሰጠው ስልጣን መካከል የመንግስትን ዳታ መሰብሰብ ነው፡፡

ኢንስቲትዩቱ የመንግስትን ዳታ ለማግኘት የሚቸገሩ የትምህርትና የምርምር ተቋማት በህግ በሰተጠው "ዳታ ሼር" ፖሊሲ መሰረት ለፈላጊውቹ ያጋራል ብለዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ የፋይናንስ ተቋማት በተለይም ባንኮች ለ"ሀርድ ዌር" መሰረተ ልማት ግንባታ ሀብትና ጊዜያቸውን ሳያባክኑ መረጃውን በኢንስቲትዩቱ የሚያገኙበትን እድል እንፈጥራለን ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የከተሞችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችል "ስማርት ሲቲ" ፕሮጀክት የመጀመሪያ መዕራፍ ተጠናቆ የፌደራል ፖሊስ ህጉን እያስፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም በአዲስ አበባ ከተማ በወሳኝ ጎዳናዎች በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አማካኝነት ቁጥጥር የሚደረግባቸው መሳሪያዎች ተገጥመዋል ብለዋል፡፡

የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የትኛውንም የመንግስትና የምርምር ተቋማት መረጃ የሚይዝ ዘመናዊ የዳታ ማዕከል መገንባቱን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ለከተሞች "ስማርት ሲቲ" ፕሮጀክት፣ የመንግስትን መረጃ ለመሰብሰብና ለሌሎች አገልግሎቶች ጭምር የሚውል ከ31 ፔታ ባይት /peta byte/ አቅም ያላው የዳታ ማዕከል ገንብተናል ብለዋል፡፡

የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ደህንነታቸው የተጠበቀ ከተሞች እንዲኖሩ፣ ችግር ፈች ጥናትና ምርምሮች እንዲካሄዱ ከተቋማት ጋር በትብብር ይሰራልም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም