በእግረኛ መንገዶች ላይ በሚቆፈሩና ክፍት በሚተው ቱቦዎች ለጉዳት እየተዳረግን ነው- አይነ ስውራን - ኢዜአ አማርኛ
በእግረኛ መንገዶች ላይ በሚቆፈሩና ክፍት በሚተው ቱቦዎች ለጉዳት እየተዳረግን ነው- አይነ ስውራን
ነሐሴ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ በእግረኛ መንገዶች ላይ በሚቆፈሩና ክፍት በሚተው ቱቦዎች ለጉዳት እየተዳረጉ መሆኑን ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ አይነ-ስውራን ተናገሩ።
በእግረኛ መንገድና በአስፋልት መንገድ ጠርዝ ላይ ለረጅም ጊዜ ክፍት የሚተው የውሃ መውረጃ ቱቦዎች እግረኞችን ለችግር ሲዳርጉ ይስተዋላል።
እንዲህ አይነት መንገዶች በተለይም ደግሞ ለአይነ ስውራን እንቅስቃሴ ፈታኝና አደገኛ ጉዳት የሚያስከትሉ ናቸው።
በዚህ ዙሪያ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ አይነ-ስውራን በእግረኛ መንገዶች ላይ በሚቆፈሩና ክፍት በሚተው የውሃ መውረጃ ቱቦዎች ምክንያት ለከፋ ለጉዳት እየተዳረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ተቆፍረው በሚተው የእግረኛ መንገዶች፣ ክፍት የሚተው ውሃ መውረጃና የፍሳሻ ማስወገጃ ቱቦዎች ገብተው ለጉዳት የታደረጉ እንዳሉ ተናግረዋል።
በአስፋልት ላይ የተጠራቀመ ውሃም ከአካል ጉዳተኞች አልፎ ለሌሎች ሰዎችና አሽከርካሪዎች ጭምር አደጋ እያስከተለ ይገኛል።
በስድስት ኪሎ አንበሳ ጊቢ አካባቢ፣ በመገናኛ፣ ከስድስት ኪሎ ወደ ፈረንሳይ መስመር ባልተከደኑ ጉድግዶች ውስጥ ገብተው ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው አይነስውራን እንዳሉ አስተያየት ሰጭዎቹ ተናግረዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አቶ ሀብታሙቴ ደረጀና አቶ አየለ ሮቤ ለተለያዩ ስራዎች ተብሎ የሚቆፈሩ እና ክፍት የሚቀመጡ ጉድጓዶች ከአካል ጉዳት ባለፈ ለሞት የሚዳርጉ አደጋዎች ስለመሆናቸውም ገልጸዋል።
በዚህ ዙሪያ በተለይም የሚመለከታቸው አካላት የእግረኛ መንገዶችን ለህብረተሰቡ በተለይም ለአይነ ስውራን እንዲመቹ በማድረግ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣንን ሃሳብ ለማካተት ኢዜአ ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም።