ለምስራቅ ኢትዮጵያ ዳር ድንበር መከበር ማንኛውንም ዋጋ እንከፍላለን - ኢዜአ አማርኛ
ለምስራቅ ኢትዮጵያ ዳር ድንበር መከበር ማንኛውንም ዋጋ እንከፍላለን
ነሐሴ 8/2014 (ኢዜአ) ለምስራቅ ኢትዮጵያ ዳር ድንበር መከበር የህይወት መስዋዕትነትን ጨምሮ ማንኛውንም የህይወት ዋጋ ለመክፈል ያላቸውን ዝግጁነት ገለጹ።
የአልሸባብ የሽብር ቡድን በኢትዮጵያ የሽብር ተግባራትን ለመፈጸም በማቀድ ሐምሌ 14 ቀን 2014 ዓ.ም በሶማሌ ክልል የተወሰኑ ጠረፋማ አካባቢዎች ሰርጎ ለመግባት ያደረገው ሙከራ ጀግኖቹ የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የሶማሌ ክልል ልይ ኃይል፣ ሚሊሻና ህብረተሰቡ ባደረጉት የተቀናጀ እርምጃ ወደ ሀገር ውስጥ የገባው የሽብር ቡድን ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን ጊዜያዊ የፀጥታ ኮማንድ ፖስት ማስታወቁ ይታወሳል።
በእርምጃው የላቀ ሚና የነበራቸው የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አልሸባብ ሀገራችንን ለመድፈር ቢሞክርም ጀግንነታችንን በማሳየት ሙከራውን አክሽፈነዋል ነው ያሉት።
ሻምበል ኒምአን አብዱላሂ እንደሚሉት፤ የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላቱ ፈንጂ እየረገጡ የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለመድፈር በሞከረው የሽብር ቡድን ላይ ከፍተኛ ርምጃ ወስደዋል።
በዚህም በርካታ የቡድኑ አባላት ሲደመስሱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ምርኮኞች፣ የነፍስ ወከፍና የቡድን መሳሪያዎች፣ መንገዶችን፣ ህንጻና ተሽከርካሪ የሚያወድሙ ፈንጂዎችንና ተቀጣጣይ ቁሶችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ተናግረዋል።
ሻምበል መሐመድ ኑሩ ልዩ ኃይሉ ጠላትን ለመደምሰስ ከፍተኛ ወኔ እንደነበረው ጠቅሰዋል።
አልሸባብ በሌሎች አገሮች የመፈጽመውም የሽብር ተግባር በኢትዮጵያ ለመፈጸም ቢያልምም የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር በመቀናጀት ህልሙን ቅዠት እንዳደረጉበት ጠቅሰዋል።
ልዩ ኃይሉን ከሦስት ዓመት በፊት የተቀላቀለው የልዩ ኃይል አባል የሱፍ አብዱላሂ በአሁኑ ወቅት አልሸባብ በተደመሰሰባቸው አካባቢዎች የቀበራቸውን ፈንጂዎች እያጸዳን ነው ብሏል።
የክልሉ ልዩ ኃይልና የአገር መከላከያ ሰራዊት ተቀናጅተው የሽብር ቡድኑን መደምሰሳቸውን የጠቀሱት አባላቱ፤ የሶማሌ ክልል ህዝብም ለሠራዊቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበርም ጠቅሰዋል።
“የኛ ድል የመጣው በህብረተሰቡ ቁርጠኛ ድጋፍ ነው” ለዚህም እናመሰግናለን ሲሉ ገልጸዋል።
አሸባሪው አልሸባብ በህብረተሰቡ ተመሳስሎ በመግባት ሽብር ለመፈጸም ቢሞክርም ህዝቡ የሽብር ቡድኑን በማጋለጥ ለፀጥታ ኃይሉ አሳልፎ እየሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።
አልሸባብን ከአገራችን አስወግደነዋል ብለን አንቀመጥም ያሉት የልዩ ኃይሉ አባላት፤ ለእናት ኢትዮጵያ ለመሰዋት ሁሌም ዝግጁ ነን ብለዋል።
አልሸባብ ጀግንነታችንን ያውቀዋል ያሉት ጀግኖቹ፤ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ አካባቢውን በትኩረት እየጠበቁ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የምስራቅ ኢትዮጵያ ዘብ መሆናቸውን ከዚህ ቀደም በፈጸሙት ጀብዱ ያስመሰከሩት የልዩ ሃይሉ አባላት፤ ወደፊትም ከአገር መከላከያ ጋር ተቀናጅተው የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስከበር ዝግጁ እንደሆኑ አረጋግጠዋል።