የካናዳ መንግስት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በጎ ምላሽ እየሰጠ ነው - የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ

53

ነሐሴ 8 ቀን 2014 (ኢዜአ) የካናዳ መንግስት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በጎ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ ገለጸ።

ዳያስፖራው እያከናወነ ባለው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ የካናዳ መንግስት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ መልካም ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ (ኢክናስ) አስታውቋል።

ኢትዮጵያን አስመልክቶ የሚወጡ ሐሰተኛ መረጃዎች በማጋለጥ በኩል አበረታች እገዛ እያበረከተ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ማርቆስ ተገኝ፤ ድርጅቱ ከተቋቋመባቸው አላማዎች አንዱ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ ስራዎች ማከናወን መሆኑን ተናግረዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ምዕራባውያን አገራት ጉዳዩን የተረዱበት መንገድ የተዛባና የተሳሳተ መሆኑን በማስታወስ በኢትዮጵያ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ሲካሄዱ መቆየታቸውን አውስተዋል።

ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የካናዳ መንግስት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ትክክለኛ እይታ እንዲኖረው የፓርላማ አባላትና ሌሎች ባለስልጣናትን በማነጋገር፣ደብዳቤዎችን በመጻፍና በማህበራዊ ትስስር ገጾች ዘመቻ በማካሄድ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ኢክናስ በቅርቡ ለካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜላኒ ጆሊ ደብዳቤ መጻፉንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ዳያስፖራው የካናዳ መንግስት በኢትዮጵያ ጠላቶች በሚተላለፉ ሐሰተኛ መረጃዎች በመሳሳት ለአንድ ወገን ያደላ አቋም እንዳይኖር ሁኔታዎችን የማስረዳትና የማስተማር ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ አቶ ማርቆስ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያን አስመልክቶ የሚወጡ ሐሰተኛ መረጃዎች በማጋለጥ እውነት እንዲወጣ እያደረግን ነው ብለዋል።

በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራው የካናዳ መንግስት በኢትዮጵያ ጉዳይ በጎ ሊባል የሚችል ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝና አሁን ላይ እውነቱን በተሻለ መልኩ እየተረዱት መምጣታቸውን አመልክተዋል።

በቅርቡም ዳያስፖራው ከካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜላኒ ጆሊ ጋር ያደረገው ውይይት ገንቢ እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢክናስ የኢትዮጵያን ጥቅም የማስጠበቅ ስራውን እንደሚቀጥልና ዳያስፖራውም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮ-ካናዳውያውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ በሕዳር ወር 2013 ዓ.ም በዳያስፖራዎች ስብስብ የተመሰረተ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም