የከተማ ወጣቶችን በዘርና በጎሳ በመከፋፈል ለማጋጨት የሚደረጉ ተግባራትን በጽኑ ይታገላል-የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር

አዲስ አበባ መስከረም 7/2011 ወጣቶችን በዘርና በጎሳ በመከፋፈል እርስ በእርስ ለማጋጨት የሚደረጉ ተግባራትን በጽኑ እንደሚታገል የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ገለጸ። ማህበሩ በዛሬው እለት ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ የከተማዋን ሰላም ለማረጋገጥና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ ወጣቶች ጋር በጋራና በአንድነት እንደሚሰራ አስታውቋል። የማህበሩ ፕሬዚዳንት ወጣት ሰለሞን ገብሩ እንደተናገረው፤ በፀረ ሰላምና ፀረ ኢትዮጵያዊ አካላት የአዲስ አበባ ወጣቶችን በዘርና በጎሳ በመከፋፈል እርስ በእርስ ለማጋጨት የሚደረጉ ተግባራት በጽኑ ይታገላል። በቅርቡ በጠፋው የሰው ህይወትና ንብረት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸው ድርጊቱ አስነዋሪና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የጎደለው ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል። ስለሆነም ሰው በመግደልና ንብረት በማውደም የተሳተፉ አካላት በህግ አግባብ እንዲጠየቁና መንግስት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል። የአዲስ አበባ ወጣቶች የሚያነሷቸዋን ጥያቄዎች በራሳቸው መንገድ እየተረጎሙ ሁኔታዎችን ለማባባስ ከሚሞክሩ ኃይሎች ወጣቶች ራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስቧል። ከተማዋ የአለም የሰላም ተምሳሌት ሆና እንድትቀጥል የአዲስ አበባ ወጣቶች በአንድነት እንደሚሰሩና በተለይ የከተማዋን ሰላም ለማረጋገጥ በአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ የኦሮሞ ወጣቶች ጋር በጋራና በአንድነት እንደሚሰሩ አረጋግጧል። የማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ወጣት አባይነህ አስማረ እንደገለጸው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ ማህበሩ ድጋፍ ያደርጋል። በአሁኑ ወቅት በከተማዋና በአገራዊ ጉዳይ፣ በይቅርታ፣ በአንድነትና በህብረ ብሔራዊነት ላይ እየመጡ ያሉ ለውጦች ዘላቂ እንዲሆኑ የአዲስ አበባ ወጣቶች የበኩላቸውን ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል። ከቡራዩና ከአካባቢዋ የተፈናቀሉ ዜጎች በዘላቂነት ወደ ቀያቸው እስኪመለሱ ድረስ የአዲስ አበባ ወጣቶች እያደረጉት ያለውን ድጋፍና እገዛ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም