የሠመራ ዩኒቨርሲቲ በአፋር ክልል በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አድርጓል

67

ነሐሴ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሠመራ ዩኒቨርሲቲ በአፋር ክልል በጦርነት ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የተለያዩ አይነት የሰብአዊ ድጋፎችን ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ማድረጉን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው "ከነሐሴ እስከ ነሐሴ በሚል መሪቃል ባለፈው አንድ አመት በተከናወኑ አበይት የስራ ክንውኖች ዙሪያ የፓናል ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር መሀመድ ኡስማን እንደተናገሩት፤ ባለፈው አንድ አመት በሽብር ቡድኑ ጥቃት ምክንያት የተፈናቀሉ በርካታ ወገኖችን መደገፍ አንዱ ቁልፍ ተግባር ነበር።

May be an image of 3 people, people sitting and indoor

ዩኒቨርሲቲው የህብረተሰቡን ችግር ለማቃለል የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸው፤ ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የሰብአዊ ድጋፍ ማድረጉን አብራርተዋል።

በመልሶ-ማቋቋም ሂደቱም ከወር በፊት በኪልበቲ-ረሱ ዞን በሚገኙ 6 ወረዳዎች ውስጥ ለሚገኙ የሰማእታት ቤተሰቦች በማህበር ተደራጅተዉ ራሳቸዉን መደጎም እንዲችሉ 10 የእህል ወፍጮ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ዩኒቨርሲቲው ድጋፉን አጠናክሮ ለማስቀጠል በጦርነቱ ያደረሰዉን ሰብአዊ፣ ቁሳዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት የሚያሳይ ዝርዝር የዳሰሳ ጥናት ማድረጉንም ገልጸዋል።

የተለያዩ አጋር አካላትን በማስተባበር ትምህርትና ጤናን ጨምሮ የማህበራዊ መሰረተ-ልማት ሴክተር ላይ ዩኒቨርሲቲው ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

በጦርነቱ ምክንያት የስነ-ልቦና ጉዳት ለደረሰባቸዉ ወገኖች የስነልቦናና ተያያዥ እገዛ በማድረግ ከገጠማቸዉ ስነ-ልቦና ችግር አንዲያገግሙም እንደሚሰራ ዶክተር መሀመድ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም