ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የሕግ ትምህርት ቤቶች ማኅበር ለሕግና ፍትሕ ስርዓት መሻሻል የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገለጸ

ነሃሴ 7/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ ለሕግና ፍትሕ ስርዓት መሻሻልና የሕግ ትምህርት ጥራት መረጋገጥ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን የኢትዮጵያ የሕግ ትምህርት ቤቶች ማኅበር ገለፀ።

የኢትዮጵያ የሕግ ትምህርት ቤቶች ማኅበር አንደኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አክብሯል፡፡

ማኅበሩ በ29 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ስር የተከፈቱ የሕግ ትምህርት ቤቶችን በአባልነት በማቀፍ ባለፈው ዓመት ነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር የተመሰረተው።

የማኅበሩ ምስረታም በመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሕግ ትምህርት ቤቶችን ትብብርና ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የመማር ማስተማር ተግዳሮቶችን በመቅረፍ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ነው።

የማኅበሩ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር ልጃለም ጋሻው፤ ማኅበሩ የሕግ ትምህርት ጥራት በማሻሻል ብቁና ተወዳዳሪ የሕግ ሙያተኞችን ለማፍራት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የሕግ ትምህርት ቤቶች ተናበውና ተቀናጅተው እንዲሰሩ በማድረግ የአገሪቱ የፍትህ ስርዓት እንዲሻሻልም እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።

በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸው፤ ነጻ የሕግ አገልግሎትንም ለአብነት አንስተዋል።

በዩኒቨርሲቲዎች ነጻ የሕግ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የሰላም ክበባትን በማቋቋምና የሕግ ባለሙያዎችን መልምሎ በማሰልጠን ብቁ የሕግ ባለሙያዎችን የማፍራት ግቡንም ጀምሯል ብለዋል።

የማህበሩ መመስረት በዋናነት በኢትዮጵያ ያለውን የሕግና ፍትሕ ስርዓት ማዘመንና የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

በቀጣይም በዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊና ጤናማ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲጠናከር የሚሰጠውን ስልጠና አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም