ቀጥታ፡

የጸጥታና የደህንነት ተቋማቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጁና የፓርቲ ወገንተኝነት የሌለባቸው መሆኑን ተገንዝበናል- የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎች

ነሐሴ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የጸጥታና የደህንነት ተቋማት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጁና የፓርቲ ወገንተኝነት የሌለባቸው መሆኑን ተገንዝበናል ሲሉ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎች ገለጹ።

ከ50 በላይ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የአየር ኃይል፣ የመከላከያ ሚኒስቴርና ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንን ጎብኝተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስተባባሪነት በተዘጋጀው የጉብኝት መርሃ ግብር ከ50 በላይ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተሳትፈዋል።

በዚህም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ የአየር ኃይል፣ የመከላከያ ሚኒስቴርና ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንን ጎብኝተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ አመራሮች በኢትዮጵያ የጸጥታና ደህንነት ተቋማት በገለልተኝነት ስራቸውን በማከናወን ላይ መሆናቸውን ተገንዝበናል ብለዋል።

በተቋማቱ ባለፉት ሶስት ዓመታት በተደረገው ሪፎርም የመከላከያ ሰራዊትና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለልተኛ ሆነው ህዝብን እያገለገሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጸጥታና የህዝብ ደህንነት ተቋማት ከፖለቲካ ፓርቲ ወይም ከሌላ አካል ጫና ነጻና ገለልተኛ መሆን ብቻ ሳይሆን የታጠቋቸው ቴክኖሎጂዎች ለህዝብ እፎይታ የሚሰጡ መሆናቸውን ተረድተናል ነው ያሉት።

የተቋማቱ የቴክኖሎጂ ዝግጁነትና የአፈፃፀም ብቃት የተሻለ ቁመና ላይ መሆናቸውን አይተናል ብለዋል አመራሮቹ።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ በርካታ ተቋማት ከስርዓቱ ጋር አብረው የሚወድቁና የሚነሱ መሆናቸውን አስታውሰው የአሁኑ የለውጥ ሂደት ግን የተቋማትን ግንባታ አጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል።

This image has an empty alt attribute; its file name is image-21.png

የጸጥታና ደህንነት ተቋማቱ አገርን በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅና የህዝቡን ደህንነት ማረጋገጥ የሚያስችል ቁመና ላይ በመገኘታቸው ተደስተናል ብለዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ብርጋዴር ጀነራል ይልማ መኳንንት፤ በመከላከያ ሰራዊት የተደረገው ሪፎርም ለሌሎች ተቋማትም ምሳሌ የሚሆን ስራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከ13 ዓመት በላይ ገንዘብ እየተበላበት የቆየው የመከላከያ ዋና መስሪያ ቤት ከለውጡ በኋላ በሶስት ዓመታት ጊዜ በሚያስደንቅ መልኩ ግንባታው መጠናቀቁን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ፤ ፖሊስ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ የሚያስችሉ ዘመናዊ  መሳሪያዎችና ቴክኖሎጂዎች መታጠቁን ገልጸዋል፡፡

"ፖሊስ ዱላ ይዞ ግብ ግብ የሚገጥም ሳይሆን ዘመናዊ መሳሪያዎችን ታጥቆ የዜጎችን ሰላም ለማስጠበቅ  የሚሰራ ሰራዊት ሆኗል" ብለዋል፡፡

በዚህም በየትኛውም አካባቢ የሚከሰቱ የጸረ ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ ተከታትሎ ለማክሸፍና ወንጀለኞችን በፍጥነት ለመቆጣጠር የሚያስችል ቁመና ገንብተናል ብለዋል፡፡   

የፌደራል ፖሊስ ሪፎርም የሰው ኃይል አቅሙን በማሳደግ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ፖሊሳዊ አገልግሎት መስጠት አስችሏል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም