ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ የግጭቱን መንስኤ የሚያጠና ቡድን ወደ ስፍራው ይልካል

አዲስ አበባ መስከረም 7/2011 ሰሞኑን በቡራዩ አካባቢ የደረሰውን ግጭት መንስኤ ለማወቅ ጥናት የሚያደርግ ቡድን ወደ ስፍራው ለመላክ ዝግጅት ማጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለፀ። ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር ዛሬ በሰጡት መግለጫ ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ዙሪያና በቡራዩ  ከተማ በደረሰው የሰው ሕይወት ማጥፋት፣ የአካል መጉደልና የንብረት ውድመት  ወንጀል መንስኤውን የሚያጠና ቡድን ወደ ቦታው ይልካል። ድርጊቱ የሰው ልጆችን በህይወት የመኖር መብትን የጣሰ፣ የአካል ደሕንነትና በነፃነት ተዘዋውሮ የመስራት ሕገ-መንግስታዊ መብትን የነፈገ በመሆኑ በዝርዝር ጥናት በማድረግ ተጠያቂነትና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ነው የገለጹት። ኮሚሽኑ በአካባቢው በደረሰው አሰቃቂ የህይወት መጥፋትና መፈናቀል የሰው ልጅን ክብር የሚያዋርድና ሕገ-መንግስታዊ መብትን የጣሰ በመሆኑ እንደሚያወግዘው ነው የተናገሩት። ከዚህ በተጨማሪም በዳውሮ ዞንም በተመሳሳይ የተከሰቱ ግጭቶችን የሚያጠና ቡድን ወደ አካባቢው የተላኩ ሲሆን በጉራጌ ዞንም በተመሳሳይ  በተለያዩ ማሕበረሰብ አካላት ዘንድ የተነሳውን አለመግባባት ለመፈተሽ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን በአስቸኳይ ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱና ሰላማዊ ኑኗቸውን እንዲቀጥሉ መንግስት ጥበቃ እንዲያደርግ የሚያስችል ምክረ ሐሳብ ለሚመለከተው አካል ማቅረባቸውንም አስታውቀዋል። ምክትል ኮሚሽነር አቶ እሸት ገብሬ በበኩላቸው ከመኖሪያ ቦታ መፈናቀል በርካታ ሕገ-መንግስታዊና ሰብአዊ መብቶችን የሚያሳጣ በመሆኑ በየደረጃው ሁሉም አካላት ሊከላከለው ይገባል ብለዋል። በመሆኑም ኮሚሽኑ በአገሪቱ የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነትን ለማምጣት የሚያካሂዳቸውን ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም