ኢዜአ ለአረንጓዴ ልማት ስኬት ከዘገባም ባለፈ በተግባር የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ ይቀጥላል- የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ

97

ነሐሴ 7 ቀን 2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ ለአረንጓዴ ልማት ስኬት ከዘገባም ባለፈ በተግባር የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ ተናገሩ።

የኢዜአ አመራርና ሠራተኞች በዛሬው እለት በእንጦጦ የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

May be an image of 4 people, people standing, tree and outdoors

የዘንድሮው የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር “ዐሻራችን ለትውልዳችን” በሚል መሪ ሃሳብ 6 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ በመሰራት ላይ ይገኛል።

ለእቅዱ ስኬት የተለያዩ ተቋማት የድርሻቸውን በመወጣት ላይ ሲሆኑ የኢዜአ አመራርና ሠራተኞችም በዛሬው እለት በእንጦጦ ችግኝ ተክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ የሚዲያ ባለሙያዎች የሕብረተሰቡ አንድ አካል በመሆናቸው በልማትም ይሁን በማህበራዊ ኃላፊነት ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በዚህ ዙሪያ ኢዜአ ኢትዮጵያ ለያዘቻቸው የልማት እቅዶች ስኬት በዘገባ ሥራዎቹ የላቀ እገዛ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የተቋሙ ሠራተኞች በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በየጊዜው እየተሳተፉ ስለመሆኑ አስታውሰው በዛሬው እለትም በእንጦጦ የችግኝ ተከላ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

የችግኞችን ተከላ ማከናወን ብቻ በቂ ባለመሆኑ ተንከባክቦ እንዲፀድቁ ማድረግ ከሁሉም የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው ብለዋል።

የኢዜአ የሕዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂያዊ አጋርነት ዳይሬክተር ዮሐንስ ወንዲራድ፤ የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በየዓመቱ በንቃት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

May be an image of 1 person, standing, tree and outdoors

በዘንድሮው የችግኝ ተከላም ከዘገባ ሥራ በተጨማሪ አሻራቸውን በማኖር ተሳትፏቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

ከኢዜአ ሠራተኞች መካከል ጋዜጠኛ ሂርጳ ሰርቤሣ፤ ከዘገባ ሥራችን በተጨማሪ በችግኝ ተከላ አሻራችንን በማኖራችን በእጅጉ ተደስተናል ብሏል።

ጋዜጠኛ ብሌን በቀለ በበኩሏ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ተንከባክበን ለማጽደቅ ዝግጁ ነን ስትል ተናግራለች።

ሌላኛዋ የተቋሙ ባልደረባ ወይዘሮ የንጉስ ውቤ፤ የተከልናቸውን ችግኞች ተመልሰን በመንከባከብ እንዲፀድቁ እንሰራለን ብላለች።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር 6 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከ7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል።

በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአራት ዓመታት በድምሩ 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል እቅድ መያዙ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም