የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 11ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

101

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 11ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ ፡፡

1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው ብሄራዊ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ረቀቂ ፖሊሲ ሰነድ ላይ ሲሆን በውይይቱም አለም አቀፍ እና ቀጠናዊ የንግድ ትስስር ለአንድ አገር የኢኮኖሚ እድገት ያለው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት፤ የንግድ ትስስሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እየተስፋፋና እየጎለበተ በመምጣቱ አገራችን ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንድትሆን አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ምክር ቤቱ አምኖበታል፡፡ በዚህ ረገድ የአገራችንን የወጪ ንግድ ስርዓት ለማሻሻል የሚያስችል፣ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስበትን ለማሳደግ፣ የወጪ ንግድ አቅማችንን ለማጎልበት እንዲሁም በዘርፉ ሰፊ የስራ እድል መፍጠር እንዲቻል በአገራችን ዋና ዋና የንግድ ኮሪደሮች የደረቅ ወደብ እንዲስፋፋና የሎጀስቲክ አገልግሎት እንዲቀላጠፍ ስርዓት መዘርጋት ወሳኝ በመሆኑ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እንዲመሰረቱ የሚያስችል ፖሊሲ መሆኑን በማረጋገጥ ግብዓቶችን በማከል በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

May be an image of 2 people and indoor

2. በመቀጠል ምክር ቤቱ ውይይቱን ያደረገው በኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን በሀገራችን አስተማማኝ የዲጂታል የመታወቂያ ሥርዓት በመዘርጋት ዜጎች እና በኢትዮጵያ ውስጥ በህጋዊ መንገድ የሚኖሩ ነዋሪዎች በሚገባ እንዲታወቁ የሚያስችል፤ በማህበራዊም ሆነ በኢኮኖሚ ዘርፍ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ከማሳለጥ እና ከማቅለል ባለፈ የአገልግሎቶችን ተአማኒነት የሚያጎለብት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን፤ በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚያገለግል ወጥ፣ አስተማማኝና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጀ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት እንዲኖር የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ መሆኑን በማረጋገጥ በረቂቅ አዋጁ ላይ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ አመልክቷል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም