ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የመልማትና የማደግ አቅም እንዳላት በግድቡ አረጋግጠናል -በኦሮሚያ አስተያየት ሰጪዎች

150

ፍቼ/ ሻሸመኔ/ መቱ/ ነገሌ / ጅማ/ግምቢ ፤ነሐሴ 7/2014(ኢዜአ) ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ለማንም ባለመበገር በራሷ አቅም የመልማትና የማደግ አቅም እንዳላት ያረጋገጠ መሆኑን በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ  የቶሬ ከተማ ነዋሪዎች መካከል  ወጣት ቢሊሱማ አሸናፊ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የህዳሴ ግድብ  በስኬት እንዲቀጥል  ባሳዩት በሳል አመራር ምስጋና ይገባቸዋል ብላለች፡፡

ከጭላማ ወደ ብርሀን በመውጣት ከድህነትና ኋላቀርነት ለመላቀቅ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  መመከያ መሆኑን ገልጻለች፡፡

የዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ በላቸው መኮንን በበኩላቸው፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ብርሀን ለጨለማ ስፍራውን የሚለቅበትና ታሪካዊ ጠላቶቻችንም የተሸነፉበት ነው ብለዋል፡፡

በተስፋ ሲጠብቁት የነበረው የሶስተኛው  ዙር የውሀ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ  መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ወደፊትም የጀመሩት ሁለንተናዊ ድጋፍና ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል፡፡

በተመሳሳይ ከፍቼ ከተማ ነዋሪዎች   ወጣት አመንቴ  በሽር በሰጠው አስተያየት፤ ሶስተኛ ዙር ውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የሚያስደስትና  የኮራንበት ነው  ብሏል፡፡

ይህም ሀገራችን በተፈጥሮ ሀብቷን በመጠቀም የዜጎችን የማደግ፣ ከድህነትና ጭለማ የመውጣት ተስፋ ያለመለመ መሆኑን ገልጿል፡፡

በግሉ  ግድቡ ለፍፃሜ እስኪበቃ ቦንድ በመግዛትና ችግኞችን በመትከል የድርሻውን እንደሚወጣም አረጋግጧል።

የፍቼ ከተማ የአባ ገዳዎች ምክር ቤት  ሰብሳቢ አቶ  ዘነበ ቱፈ በበኩላቸው፤ የውሃ ሙሌቱ በአባይ ወንዝ ዙሪያ የኖረውን ኢ-ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማስተካከል አዲስ ምዕራፍ የከፈተና ለአፍሪካ ህዝቦች የልማት አርኣያ የሆነ ነው ብለዋል፡፡

ግድቡ ኢትዮጵያውያን በአንድነትና በትብብር ከሰሩ የማልማት አቅም እንዳላቸው ያረጋገጠ ሀቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ አፍራሽ አመለካከቶችን  ከመታገል ባለፈ ለግድቡ ግንባታ ከወር ደመወዛቸው በማዋጣት፣ ቦንድ በመግዛትና ህብረተሰቡን በማነቃቃት እንደሚሳተፉም አስታውቀዋል፡፡

የውሃ ሙሌቱ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናን በመቋቋም የኢትዮጵያውያንን አንድነትና በይቻላል መንፈስ ሰርቶ ማሳየትን  በተግባር ያሳየ ነው ያሉት ደግሞ መምህር  ታምሩ ቶልቻ ናቸው  ፡፡

ይኸም በራስ አቅም ተማምኖ ስራ መጀመርንና መጨረስ እንደሚቻል የሚያሳይ በመሆኑ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል   የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪው አቶ  ሮቤ ኢዳሶ ፤  ግድቡ ኢትዮጵያውያን   በአንድነት እና መተባበር በዐድዋ ድል እንደ አደረጉ ሁሉ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ በመድገም አይበገሬነታችንን አስመስክረናል ብለዋል።

 የግድቡ የድል ብስራት ኢትዮጵያ  በራሷ አቅም  መልማት እንደምትችል  ለአለም ሁሉ  ግልፅ ያደረገ መሆኑን  ገልጸዋል።

 አቶ አብዱረህማን ነሜ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያውያን  የአንድነት እና ቁርጠኝነት ካስመዘገበው ከዚህ  የልማት ድል ልምድ  በመቀስም በመቻቻልና በመደጋጋፍ  ሌሎችንም ልማቶች አጠናክረን ከድህነት ለመውጣት መትጋት ይኖርብናል ብለዋል።

ከዚህ በፊት ከነ ቤተሰባቸው ጨምር ለግድቡ  ቦንድ ሲገዙ እንደነበው አስታውሰው፤  ፣ ግንባታው እስከሚጠናቀም ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በተያያዘ ዜና ከመቱ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ እሸቱ በቀለ በሰጡት አስተያየት፤ ሶስተኛው  ዙር የሕዳሴ ግድቡ የውሃ ሙሌት በሰላምና በስኬት መጠናቀቅ መደሰታቸውን ገልፀው፤ በብዙ ሀገራዊ ፈተና ውስጥ ሆነን ይህን ማሳካታችንም የመንግስትን ጥንካሬና ቆራጥነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሐቢብ ቡልቻ ፤ በብዙ ፈተና ውስጥ ሆነን ፕሮጀክቱን ማስቀጠልና ማሳካት መቻላችን ትልቅ ደስታን የፈጠረልን የኢትዮጵያውያን ሁሉ ድል ነው ሲሉ ገልጸዋል።

መንግስትም ለፕሮጀክቱ የሰጠው ትኩረትና ያሳየው  ቆራጥነት  የሚያስመሰግነው ነው ብለዋል።

መምህርት አሻ ኢድሪስ በበኩላቸው፤ "የሶስተኛው ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ ለመላው ኢትዮጵያውያን ትልቅ ደስታችን ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በምዕራብ ወለጋ የግምቢ ወረዳ ነዋሪ አቶ ምረቱ መላኩ በሰጡት አስተያየት፤  በአብሮነት ሁሉም ከተሳተፉ ሃገራችን የገጠማትን ፈተና ለማለፍና ሉዓላዊነቷን ለማስከበር አቅም እንዳለን የግድቡ ሶስተኛው ዙር የዉሃ ሙሌት ስኬት  አስተምሮናል ብለዋል፡፡

የግድቡ ሶስተኛው ዙር የዉሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ   አቶ   ሓምብሳ መኮንን ናቸው።

ግድቡ ሙሉ በሙሉ እስከሚጠናቀቅም ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ አስተያየት ሰጪዎቹ አስታውቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ  ከጅማ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ታምራት በቀለ እንዳሉት፤ የሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ  ጠላትን የሚያሳፍር፤  ወዳጅን የሚያኮራ ታላቅ ደስታ ነው።

ኢትዮጵያዊያንን በአንድነት ያስተሳሰረ ፣ በደስታ ያሰከረ፣ ብሔራዊ ስሜታችንን በአንድነት የገለጽንበት የታሪክ አጋጣሚ ነው፤  መንግስት ህዝቡን በማስተባበር ከዚህ የበለጠ ስኬት ማስመዝገብ እንደሚቻል ያመላከተ ነው ብለዋል።

ዋና ኢንስፔክተር  ገዛኸኝ አውግቸው በበኩላቸው፤  የግድቡ ሁለተኛ ተርባይን ሀይል ማመንጨትና በሶስተኛው የውሃ ሙሌት በመጠናቀቁ  መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የግድቡ ስኬት ኢትዮጵያ ለማንም ባለመበገር በራሷ አቅም  የመልማትና የማደግ አቅም  እንዳላት ያረጋገጠ መሆኑን  የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ የኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበትና የአንድነት ማጠናከሪያ የሆነውን የሕዳሴ ግድብ  ለማጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናከር እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም