በአዲስ አበባ ዙሪያ በዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት በማውገዝ የተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ዙሪያ በዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት በማውገዝ የተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ
አዲስ አበባ መስከረም 7/2011 በቡራዩ፣ ከታና በሌሎችም የአዲስ አበባ አካባቢዎች የደረሰውን ጥቃት በማውገዝ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። ሰልፈኞቹ ዘረኝነትና ብሔር ላይ ማተኮር ይቁም፣ ፍትህ ለወገኖቻችን፣ መንግስት ጥፋተኞች ላይ ህጋዊ እርምጃ ይውሰድ የሚሉና ሌሎችንም መፈክሮች በመያዝ መዳረሻቸውን ወደ አራት ኪሎ ቤተ-መንግስት በማድረግ ከተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የተቃውሞ ሰልፍ ተሳታፊዎች እየደረሰ ያለው ዘረኝነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንዲቆም፣ ጥቃት የሚያደርሱትንም መንግስት በአስቸኳይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠይቀዋል። ከአስተያየት ሰጭዎች መካከል አቶ ተክሎ ተስፋዬ እንዳሉት መንግስትን ህዝቡን ወደ መደመርና አንድነት እየሰበሰበ ባለበት ሰዓት ሰብዓዊ ባልሆነ ሁኔታ ብሄር ተኮር ጥቃት በመፈጸሙ መንግስት ፍትህ እንዲሰጥበትና ለሚመለከተው ሁሉ ጩኸታችንን ለማሰማት ሰልፍ መውጣታቸውን ገልጸዋል፡፤ "የኢትዮጵያ ህዝብ ያለውን ተካፍሎ የሚኖር ነው። ሁሉ ነገር የራሱ ትእግስትና ልክ አለው። ስለዚህ እኛ ፍትህ እንፈልጋለን።መንግስት እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን" ሲሉ አተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ አገርነሽ አዲቶ ናቸው፡፡ ውድነሽ የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው"እኛ ሰርተን መኖር ነው የምንፍልገው።ጥቃት ሊደርስብን አይገባም፤ በአገራችን ንብረት ማፍራት አንችልም! ፍትህ ልናገኝና መብታችን ሊከበር ይገባል ብለዋል ። በተፈጠረው ግጭት የተጠረጠሩ ከ70 በላይ ሰዎች እስከ ትናንት ድረስ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የገለጸ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች የሚደግፍ ኮሚቴ መዋቀሩን አስታውቋል።