የጀርመኑ አንሃልት ዩኒቨርሲቲና ጅማ ዩኒቨርሲቲ የባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ትምህርትን ለማጠናከር የፕሮጀክት ስምምነት ስነድ ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የጀርመኑ አንሃልት ዩኒቨርሲቲና ጅማ ዩኒቨርሲቲ የባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ትምህርትን ለማጠናከር የፕሮጀክት ስምምነት ስነድ ተፈራረሙ

ጅማ፣ ነሐሴ 06/2014(ኢዜአ) በጀርመን አንሃልትና በጅማ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ትምህርትን ለማጠናከር የሚያስችል የፕሮጀክት የስምምነት ስነድ ተፈረመ።
"የፕሮጀክቱ ዋና አላማም በጅማ ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ የባዮሜዲካል ምህንድስና ትምህርትን ማጠናከርና የተሻለ የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት የሚያግዝ ነው" ተብሏል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ በስምምነቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ፕሮጀክቱ የጤና አገልግሎቱን ተግዳሮት ለመፍታት የሚረዳና ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም "በትብብርና በአጋርነት እንዲሁም የሀሳብ ልውውጥ በማድረግ እስካሁን የተገኘውን ውጤት ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ ያስችለናል "ብለዋል።
የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር ቦሪስ ብራሲዮ ስለ ፕሮጀክቱ ባደረጉት ንግግር ባዮሜዲካል ምህንድስና ከተለያዩ የምህንድስና ዘርፎች አንዱ መሆኑን ገልጸው በጤናው ዘርፍ የጎላ ሚና ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
በፕሮጀክቱ ሁለቱ ተቋማት የልምድ ልውውጥና በጤናው ዘርፍ የሚሰጠውን የስልጠናና ትምህርት መርሀግብር ለማሻሻል ታልሞ የሚተገበር መሆኑን ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስቴርን በመወከል የተገኙት ዶክተር አሰግድ ሳሙኤል በበኩላቸው ለህብረተሰብ ጤና ትኩረት የሚሰጡ የፕሮጀክት ፕሮግራሞችን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ዶክተር አሰግድ አክለውም መንግስት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለህክምና ቁሳቁስ መግዣ እያዋለ መሆኑን ጠቅሰው "በጥገናና በማኔጅመንት ባለሙያዎችን በመላክ ድጋፍ እናደርጋለን" ብለዋል።
ለፕሮጀክቱ ስኬት ሁሉም በባለቤትነት ስሜት በአጋርነትና በትብብር በመስራት የታለመለት ግብ እንዲሳካ የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ በተደረገው የባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ፕሮጀክት ማስጀመርያ መርሀ ግብር የተለያዩ የዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች፣ የክላስተር ዩኒቨርሲቲ ተቋማት ተወካዮች ፣ የባዮሜዲካል ኢንጂነሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።