የተጀመረውን የለውጥ አጀንዳ የሚያደናቅፍ ተግባር ተቀባይነት የለውም- ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ - ኢዜአ አማርኛ
የተጀመረውን የለውጥ አጀንዳ የሚያደናቅፍ ተግባር ተቀባይነት የለውም- ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ
ባህርዳር መስከረም 7/2011 የተጀመረው የለውጥ አጀንዳ ወደ ፊት እንዳይራመድ በተለያዩ ቡድኖች እየተፈፀመ ያለው የድርጅትና የህዝቦችን መብት የሚጋፋ ተግባር ተቀባይነት እንደሌለው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲ ንቅናቄ/ብአዴን/ አስታወቀ። ድርጅቱ ወቅታዊ ጉዳዮች አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው የለውጥ እንቅስቃሴው አወንታዊ በሆነ አቅጣጫ ወደፊት እንዳይራመድ የሚፈልጉ የቆየ የጥላቻ ፖለቲካ አራማጅ ቡድኖች እየተከተሉት ያለው አቅጣጫ የሚያወጣ አይደለም ። "በህዝብ ትግልና መስዋትነት የተገኘው ነፃነትና የዴሞክራሲ ተስፋ መልሶ እዲጨልም ቀን ከሌት የሚታትሩ ቡድኖችም ሆነ አካላት ወደ ትክክለኛ መስመር ሊመለሱ ይገባል" ብሏል። በለውጥ ኃይል ስም ተሸፍኖ ህግና ስርዓት ባልተከተለ መንገድ የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ስራ ለማደናቀፍና ለውጡን በብቃት እየመሩ የሚገኙ የድርጅቱ አመራሮችን ለውጥ አደናቃፊ በማለት ለመፈረጅ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደሌላው ድርጅቱ በመግለጫው አመልክቷል ። "አመራሩ በተጨባጭ ለህዝብ እያበረከተ ካለው አስተዋጽኦ ይልቅ በትውልድ ቦታና በዘር ሃረግ በመከፋፈል እንዲሁም ስም በማጥፋት የለውጡን ግስጋሴ በሚጎዳ አኳኋን የሚደረገው እንቅስቃሴ ሊቆም ይገባል" ብሏል። ድርጅቱ የራሱ የሆነ ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ስርዓት እንዲሁም አመራር የሚመድብበትና የሚያወርድበት ግልፅ አሰራር እንዳለው መግለጫው አመልክቶ ህዝብ ያላመነባቸውንና የአሰራር ክፍተት ያለባቸው አመራሮች ላይ የማስተካከያ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታውቋል ። ከዚህ ውጭ በሆነ መንገድ ማንኛውንም አመራር የለውጥ አደናቀፊ የሚል ስም በመስጠት ከኃላፊነት እንዲወገድ የሚደረገው ግፊትና ዘመቻ ተገቢነት እንደሌለው የድርጅቱ መግለጫው ጠቅሷል ። "ህዝባችን ለፍትህና ለዲሞክራሲ ታገለ እንጂ ስርዓት አልበኝነትን ለማንገስ መስዋትነት አልከፈለም" ያለው መግለጫው በክልሉ የሚከናወንውን የግብይት ስርዓት በህገ ወጥ መንገድ ለማደናቀፍ እየተደረገ ያለው ሙከራም በፍጥነት ሊቆም እንደሚገባም አሳስቧል። "በህዝቦች መካከል ሰላም፣ ይቅርታና ፍቅር እንዲሰፍን መላ የሃገራችን ህዝቦች ሌት ተቀን በሚተጉበት በዚህ ወቅት በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከለ ዞን ጉባ ወረዳ አልመሃል በተባለ አካባቢ የተፈፀመውን ግድያም ብአዴን በፅኑ ያወግዘዋል" ሲል በመግለጫው አስታውቋል ። በዚህ ድርጊት የተሳተፉ ብቻ ሳይሆን ይህንኑ ኢ- ሰብአዊ ድርጊት እንዲፈፀም ስምሪት የሰጡ አካላት ጭምር በህግ እንዲጠየቁ ድርጅቱ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በጥብቅ እየሰራ መሆኑን ገልጿል። በክልሉ ውስጥም ዜጎችን በማንነታቸውና በያዙት ፖለቲካዊ አቋም በመመስረት የንብረት ውድመትና ዘረፋ እንዲሁም ማንኛውንም ጥቃት በሚፈፅሙ ኃይሎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ አመራር መሰጠቱንም ድርጅቱ በመግለጫው አብራርቷል። የየለውጥ እንቅስቃሴው ተጠብቆና ዘላቂ ሆኖ ሀገሪቱን ወደ ዳበረ ዴሞክራሲ ስርዓት ለማሸጋገር ይቻል ዘንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል ። በህዝብ ግፊትና በድርጅቱ መሪነት የተቀጣጠለው ለውጥ ለውጤት እንዲበቃ የክልሉ ህዝብ፣ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች፣ እንዲሁም የፀጥታ አካላት ሰላም በማስፈንና የህግ የበላይነትን በማስከበር የተለመደውን ሚናቸውን እንዲወጡ ብአዴን በመግለጫው ጠይቋል ።