የዓባይ ወንዝ ሙላት ስጋት፤ በዓባይ ግድብ ሙሌት ብሥራት

111

አየለ ያረጋል-ኢዜአ

ኢትዮጵያ የምድራችንን ለግላጋውን ወንዝ፣ ንጉሠ-ነገሥት ዘአፍላገተ ዓለም ዓባይ ወለደች። ዓባይ ግን እንደ በኹር ልጅነቱ ወላድ እናቱን አልካሰም። ግብሩ ጉዞ ሆነ፤ ኑሮው ዙረት። ቀለሙና ድንፋታው የኢትዮጵያ ሸለቆዎች ዕንባ ነው። ኢትዮጵያ ‘የወላድ መካን’ ይሏት ነገር ‘የዓባይ ልጅ ውሃ ጠማው’ ተባለ። ልጇ ዓባይም በ‘ዓባይ ማደሪያ ቢስ ግንድ ይዞ ይዞራል’ ብላ ረገመችው። የዓባይ ሥነ-ቃል፣ ትውፊትና ይትባሀል በቁጭት፣ እንጉርጉሮና ወቀሳ ዜማዎች ተቃኘ።

የዓባይ ሙላት ለአገሬው ጦስ እንጂ በረከት ጠብ አላደረገም። በወርሀ ክረምት ዓባይ እስከ ጥግ በሙላት ይገማሸራል። በወርሀ ክረምት ሙላቱ እየተገማሸረ፣ በወርሀ በጋ እየለዘበ ቁጣውና ትህትናው እየተፈራረቀ ዘመናትን ተሻግሯል። የሊቃውንትና ጠቢባን አርዕስት፣ የአገሬው ስነ-ቃል ቅኝትም ዓባይ የሞላ ዕለት ‘የጉደል’ ተማጽኖ ነው። የዓባይ ሙላት የጀግንነትና አይደፈሬነት ትዕምርት ነው። ወርሀ ክረምት በባተ ቁጥር ስጋት ዓባይ ሙላት ለአገሬው ሕዝብ ስጋት ነው። ሰውና እንስሳቱን ይነጥቃል፤ የተነፋፈቀ ዘመድ ያራርቃል። የማዶ ለማዶ ማኅበረሰብን ማህበራዊ መስተጋብር ይጋርዳል። ክረምቱ ለአገሬው ስጋት፣ ፍርሃትና ብሶት ሆኖ ከርሟል።

የእስከዛሬ ዓባይ ፍሰት ለባለቤቱ ባዳ፣ ለባዕዳን እንግዳ ቢሆንም የዓባይ ልጆች ለዕልፍ ዘመናት ዓባይን ለቁም ነገር ተመኝተውታል። የዓባይ ውሃ ጠላ ሆኖ እንዲጠጣ፣ መና ሆኖ እንዲጎረስ፣ ሲሳይ ሆኖ እንዲቆረስ የእልፍ ኢትዮጵያዊያን ምኞት ነበር። በትችትና ምኞት፣ በተስፋና ወቀሳ የተወገረው የአባይ ወንዝ ግንድ ይዞ ዟሪነቱ ሊገታ፣ የልጅ ባዕዳነቱ ሊያከትም፣ ማደሪያ ቢስነቱ ሊቆም ... የተወጠነው በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጥንስስ ነበር። ይህ ግድብ እንደ ማንኛውም ግድብ አይደለም። በሕዝብ የድጋፍ ማዕበል ታጅቦ፣ በጠላት ዐይን ተገርምሞ፣ ዳፋና ተግዳሮቶች የተሻገረ ዳግማዊ አድዋ የሚሰኝ ከግድብ በላይ የሆነ ፕሮጀክት ነው።

ግድቡ ከሦስት ዓመታት በፊት የውሃ ሙሌት ጀምሯል። በዘንድሮ ክረምት ዝናብ ሦስተኛው የግድቡ ሙሌትም ተጠናቋል። የዘንድሮና የድሮ ክረምት በኢትዮጵያዊያን ጆሮ ያለው ስሜት በዓባይ ወንዝ ሙላትና በዓባይ ግድብ ሙሌት ሁነቶች ሳቢያ ተቀይሯል። የድሮ ክረምት ለአገሬው ጆሮ አበሳ፤ ዘንድሮ ደግሞ በ‘ጉሮ ወሸባ’ ዜማ ተተክቷል። በአጭሩ የዓባይ ወንዝ ውሃ ሙላት ስጋት፣ በዓባይ ግድብ ውሃ ሙሌት ብሥራት ተተክቷል። በቃ ታሪክ ተቀየረ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ብቻ አይደለም ድሉ። ግድቡ ከ11 ዓመት በኋላ በሸኘነው በጀት ዓመት ካሉት 13 ተርባይኖች መካከል በአንደኛው ተርባይን የተስፋ ፍሬው ተቀምሷል። ባሳለፍነው ወርሀ-የካቲት ኃይል ማመንጨቱ ይታወሳል። ሁለተኛው ተርባይንም  ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ተበስሯል። ሦስተኛው ዙር ውሃ ሙሌትም ተከውኗል። ያም ሆኖ ዓባይ ተቀመሰ እንጂ የኢትዮጵያን የዘመናት ረሀብና ጥማት ግን ገና አላረካም።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ርዝመቱ 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ነው። የግድቡ ጠርዝ ከባህር ጠለል በላይ 645 ሜትር ከፍታ ሲሆን የግድቡ ቁመት ብቻውን 145 ሜትር ይረዝማል፡፡ ትልቁ የኮንክሪት ግድብ ከፍታ 645 ሜትር ነው። ውፍረቱ ከግርጌ 130 ሜትር፤ ከራስጌ/ጫፍ 11 ሜትር ነው።

የግድቡ የቦታ ስፋት 1 ሺህ 680 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ነው፤ 74 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መጠን ይይዛል። ሁሉም ተርባይኖች ሥራ ሲጀምሩ ከ5 ሺህ በላይ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል። ይህም በአፍሪካ ትልቁ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ያሰኘዋል። ከ375 እስከ 400 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ 13 የኃይል ማመንጫ ዩኒቶች አሉት።

ግብጽ ግድቡ በመገንባቱ ወደ ግዛቷ የሚፈሰው የውኃ መጠን ይቀንስብኛል በሚል ሰበብ ኢትዮጵያ ከወንዟ እንዳትጠቀም ለዘመናት የሄደችበትን ኢ-ፍትሃዊ ትግል የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዕውን እንዳይሆን የተቻላትን ሁሉ ስታደርግ ቆይታለች። አንዳንድ ምዕራባዊያን፣ የተፋሰሱ የታችኛው አገራትና የአረብ ሊግ አገራት በግድቡ ዙሪያ መልከ በዙ ተቃውሞና ጫጫታ አሰምተዋል። የግብፅን የውሃ ዋስትናን በሚያስከብር መልኩ “አሳሪ ሕጋዊ ስምምነት እንዲደረስ” የኢትዮጵያ ጠላቶች ፍላጎት ነው። ያም ሆነ ይህ ግን ፕሮጀክቱ መፈጸሙ አይቀርም።

ኢትዮጵያ በበኩሏ ግድቧ ከድህነት መውጫ፣ የዜጎቿን ተጠቃሚነት ማረጋገጫ እንጂ የተፋሰሱን ሃገራት እንደማይጎዳ አበክራ አሳስባለች። 86 በመቶ የሚሆነውን የዓባይ ወንዝ ውሃ በምትለግሰው ኢትዮጵያ 60 በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያዊያን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ አይደለም። በሚሊዮን የሚቆጠረው ሕዝቧ ከድቅድቅ ጨለማ ለማውጣት ግድቡ መሙላት፣ ኃይል ማመንጨት የቅንጦት ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ይሆናል። የዓባይ ወንዝ ሙላት ስጋት፤ በዓባይ ግድብ ሙሌት ብሥራት በኤሌክትሪክ ብርሀን ፍካትይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም