ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ በፍትሃዊነት መጠቀም እንደሚቻል ለዓለም በማሳወቅ እዚህ ደርሳለች- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

95

ነሐሴ 6 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ በፍትሃዊነት መጠቀም እንደሚቻል በዓለም አደባባይ አቋሟን እያሳወቀች እዚህ ደርሳለች ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

አቶ ደመቀ ይህን ያሉት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በድል መጠናቀቅ ማብሰሪያ ላይ በጉባ በተገኙበት ወቅት ነው።

የአባይን ውሃ በፍትሃዊነት መጠቀም እንደሚቻል ኢትዮጵያ በእውነትና በፍትሃዊነት በአለም አደባባይ አቋሟን እያሳወቀች እዚህ ደርሳለች ብለዋል።

ለተለያዩ ፍላጎቶች የኢትዮጵያን የፍትህ መንገድ በመጫን ለማዛባት ወደ ቀድሞ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶች አንስተዋል።ይሁን እንጂ ጥረቶቹ ከእውነት ያፈነገጡ የኢትዮጵያውያንን መብት የሚጋፋ በመሆናቸው ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ተናግረዋል።

"የተፈጥሮ ጸጋ በተፈጥሮ ሁላችንንም ያስተሳሰረ እንደመሆኑ በመተባበርና መደማመጥ የበለጠ ሁላችንም እንጠቀምበታለን" ሲሉም አክለዋል።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማሳወቅ፣ በገንዘብ፣ በእውቀትና በሌሎች በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም ለአገር ግንባታ በአንድነትና በመተባበር መቆም እንደሚገባ ጠቁመው ቀሪ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ድጋፍና ንቅናቄ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም