ሰራዊቱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በደምና በአጥንቱ ያስከብራል--ሌተናል ጀነራል ዘውዱ በላይ - ኢዜአ አማርኛ
ሰራዊቱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በደምና በአጥንቱ ያስከብራል--ሌተናል ጀነራል ዘውዱ በላይ
ሰቆጣ ነሐሴ 6/2014 ዓ/ም /ኢዜአ/ ''የኢትዮጵያዊያን የሀልውና እስትንፋስ የሆነውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ሰራዊቱ በደምና አጥንቱ ያስከብራል ሲሉ በሃገር መከላከያ ሰራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ዘውዱ በላይ አስታወቁ።
የዕዙ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ዘውዱ በላይ የግድቡ ሁለተኛው ተርባይን የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት መጀመርን አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት የታላቁ ህደሴ ግድብ በመላው ኢትዮጵያውያን ርብርብ በሃገራዊ ወኔ የተገነባ ነው።
''ሃገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ሃብት ምንጭ ባለቤት ናት'' ከዚህም አንዱ ታላቁ ወንዛችን አባይ ነው" ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድባችን ሁለተኛው ተርባይን ሃይል ማመንጨት መጀመሩ የህዝቡን የይቻላል መንፈስ በከፍተኛ እምርታ ያሳደገ እንደሆነም ተናግረዋል።
እንደ ሌተናል ጀነራል ዘውዱ የህዳሴው ግድብ አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲበቃ ሰራዊቱ የራሱን አሻራ ማሳረፉን ጠቁመው ሰራዊቱ ለግድቡ ግንባታ ከደመወዙ ላይ ቀንሶ በመስጠት ጭምር የድርሻውን ማበርከቱን አመልክተዋል ።
ሰራዊቱ ግድቡን ሌት እና ቀን ያለምንም መታከት ከጠላቶች በአይነ ቁራኛ ሲጠብቅ መቆየቱን ተናግረዋል።
እንደ ስሙ ታላቅ የሆነው የህዳሴው ግድብ ለኢትዮጵያ ህዝብ ግድብ ብቻ ሳይሆን የህልውና እስትንፋስ በመሆኑ ሰራዊቱ በደምና በአጥንቱ ሲያስከብረው ይኖራል" ሲሉ ሌተናል ጀነራል ዘውዱ በላይ አስታውቀዋል።
የታላቁ ህደሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን በትናንትናው እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት ሃይል ማመንጨት መጀመሩን ይታወቃል።