ኢህአዴግ ስሙንም ሆነ አርማውን የመቀየር ሀሳብ እንደሌለው አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ኢህአዴግ ስሙንም ሆነ አርማውን የመቀየር ሀሳብ እንደሌለው አስታወቀ
አዲስ አበባ መስከረም 7/2011 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ስሙንም ሆነ አርማውን የመቀየር ሀሳብ እንደሌለው አስታወቀ። የኢህአዴግ 11ኛ መደበኛ ጉባዔ ከመስከረም 23 እስከ 25 ቀን 2011 ዓ.ም በሀዋሳ ይካሄዳል። የጽህፈት ቤቱ ዓላፊ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብርእግዚአብሄር ጉባዔውን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ድርጅቱ እንደሌሎች ብሄራዊ ድርጅቶች ስሙንም ሆነ አርማውን የመቀየር ሀሳብ እንደሌለው አስታውቀዋል። ከዚህ ሌላ ድርጅቱ ቀደም ሲል ሲያራምድ የነበረውን ርዕዮተ ዓለም እንደሚቀጥልበትና እያደገ የሚሄድ ድርጅት እንደመሆኑ መጨመር ያለባቸውን ነገሮች እየጨመረ እያደገ የሚሄድ መሆኑን ገልጸዋል። ወቅታዊውን የአገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ መሰረት በማድረግም አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ብለዋል። የድርጅቱ 10ኛ መደበኛ ጉባዔ ነሀሴ 2007 ዓ.ም መካሄዱ ይታወሳል። 11ኛ መደበኛ ጉባዬው መጋቢት 2009ዓ.ም መካሄድ የነበረበት ቢሆንም የአገሪቷንና የድርጅቱን ወቅታዊ ሁኔታ በመገምገም ጉባዔው እንዲራዘም መደረጉን ወይዘሮ ፈትለወርቅ ተናግረዋል። በድርጅቱ ህገ ደንብ መሰረት መደበኛ ጉባዔን በስድስት ወር ማራዘም እንደሚቻልና ለጉባዔው በቂ ዝግጅት ለማድረግ እንደተራዘመም ገልዋል። ጉባዔው ከሚያተኩርባቸው የውይይት አጀንዳዎች መካከል በ10ኛው የድርጅቱ ጉባዔ ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች መገምገም፣ ድርጅቱ በመጋቢት ወር ያደረገውን የአመራር ለውጥ በተመለከተ የመጡ ለውጦችና ለውጦቹን ለማስቀጠል ምን መደረግ አለበት በሚል በተዘጋጀ የውይይት መነሻ ላይ ውይይት ማድረግ ይገኙበታል። ባለፉት ሶስት ዓመታት የተሰሩ ስራዎች ዝርዝር ሪፖርትም ቀርበው ውይይት ይደረግበታል። በድርጅቱ 12ኛ ጉባዔ የሚከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል። ''በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ የለውጥ እንቅስቃሴውን በማስቀጠል የኢትዮጵያ ህዳሴን እናረጋግጥ" በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው በዚህ ጉባዔ ከእያንዳንዱ ብሄራዊ ድርጅት 250 ተወካዮች በአጠቃላይ አንድ ሺ አባላት በድምጽ ሰጪነት ይታደሙበታል። በሌላ በኩል በታሳቢነት የሚሳተፉ የተለያዩ አካላት እንደሚሳተፉም ታውቋል።