የኢፌዲሪ አየር ኃይል የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥንና በሕዝቡ ዘንድ የባለቤትነት ስሜት የሚፈጥር ሪፎርም አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የኢፌዲሪ አየር ኃይል የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥንና በሕዝቡ ዘንድ የባለቤትነት ስሜት የሚፈጥር ሪፎርም አድርጓል
ነሐሴ 6 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢፌዲሪ አየር ኃይል የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥንና በሕዝቡ ዘንድ የባለቤትነት ስሜት የሚፈጥር ሪፎርም ማድረግ መቻሉን ማየታቸውን የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎች ተናገሩ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመቻችነት ከ50 በላይ የተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎች የኢፌዲሪ አየር ኃይልን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፖርቲ ኃላፊዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ለረዥም ዓመታት የኢትዮጵያ አየር ኃይል በጠንካራ ተቋምነቱ የሚታወቅ ነበር።
ሆኖም በኢትዮጵያ ለዘመናት እንደ ልምድ ሆኖ የቆየው ተቋምን አፍርሶ የመገንባት አባዜ ይህንንም ተቋም ዋጋ አስከፍሏል ነው ያሉት።
የኢፌዲሪ አየር ኃይል በ93 ዓመታት የታሪክ ሂደቱ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ቢሆንም ባለፉት ሩብ ክፍለ- ዘመናት በሰው ኃይልና ትጥቅ እንዲዳከም ተደርጎ ነበር ብለዋል።
በጉብኝታቸው የኢፌዲሪ አየር ኃይል የኢትዮጵያን ታላቅነት በውል ተገንዝቦ ለሕዝቡ ታሪክ የሚመጥንና የባለቤትነት ስሜት የሚፈጥር ሪፎርም ማድረጉን መታዘባቸውን ተናግረዋል፡፡
አየር ኃይሉ ታሪክ፣ ባህልና እሴቱን ጠብቆ ለትውልድ የሚተላለፍ የሕዝብ ሀብት መሆኑን አሳይቷልም ነው ያሉት።
የፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎቹ የተደረገው ተቋማዊ ሪፎርም በሕዝቡ ዘንድም እምነት የሚጣልበት ተቋም እንዲሆን ያስችለዋል ብለዋል፡፡
የኢፌዲሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው፤ ''ተቋሙ የመላው ኢትዮጵያዊያን የጋራ ሀብት ነው'' ብለዋል፡፡
አየር ኃይሉ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት የሰው ኃይሉንና የቴክኖሎጂ አቅሙን በማሳደግ የኢትዮጵያን አየር ክልል በንቃት እየጠበቀና እየተከላከለ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰራዊቱ ውስጥ ጣልቃ ሳይገቡ የሰከነ ፖሊቲካ በማራመድ ውስጣዊ ሰላምና አንድነትን ለመፍጠር ቢተጉ መልካም መሆኑንም አንስተዋል፡፡
''ይህ ሲሆን የኢፌዲሪ የአየር ኃይል ሸክሙ ይቀልለታል፤ ሌሎች አገራዊ ተልዕኮዎችን በብቃት ለመፈጸም ተጨማሪ ጉልበት ያገኛል'' ብለዋል፡፡