ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የአየር ክልሉን ከማንኛውም ጥቃት መጠበቅና መከላከል የሚያስችል ቁመና ላይ መሆኑን ገለጸ

 ነሐሴ 6/ 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር ኃይል የአገሪቷን አየር ክልል ከማንኛውም ጥቃት መጠበቅና መከላከል የሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ የአየር ኃይሉ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከ93 ዓመት በፊት በአፍሪካ የመጀመሪያ አየር ኃይል ሆኖ የተመሰረተ አንጋፋ ተቋም ነው።

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ነሐሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም 'ጃን ሜዳ' ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ምስረታ ከተበሰረ በኋላ በ1954 ዓ.ም በኮንጎ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ የጎላ ተሳትፎ ማድረጉም ተመልክቷል፡፡

የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አየር ኃይሉ ቴክኖሎጂ በማፍለቅና የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት በ2022 ዓ.ም ከአፍሪካ ቀዳሚ የአየር ኃይል የመሆን ራዕይ ሰንቋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላት ቀደም ባሉት ዓመታት በፖለቲካ አመለካከት እና በብሔር ማንነት ተከፍለው አየር ኃይሉ ችግር ውስጥ ወድቆ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡   

ከለውጡ በኋላ ግን ይሄንን አስተሳሰብ በመቀየር የሰራዊት አባል ሁሉ ከፖለቲካና ከብሔር አስተሳሰብ እንዲወጣ በማድረግ ኢትዮጵያዊ መልክ ያለው አየር ኃይል መገንባት ተችሏል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን የተለያየ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥና የተለያየ አየር ጸባይ መቋቋም የሚችል ሰራዊት መገንባት የሚያስችል ጸጋ ያላት አገር መሆኗንም አንስተዋል፡፡

በዚህ ወቅትም የኢፌዴሪ አየር ኃይል "ለታላቅ አገር ታላቅ የአየር ኃይል" በሚል መሪ ሀሳብ የዘመኑን ቴክኖሎጂ የሚረዳ የሰው ኃብት፣ ዘመናዊ ትጥቆችና የውጊያ መሰረተ ልማት አሟልቷል ብለዋል፡፡

ሌተናል ጀነራሉ የኢፌዴሪ አየር ኃይል የአየር ክልሉን ከማንኛውም ጥቃት መጠበቅና መከላከል የሚያስችል የተሟላ ቁመና ላይ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ሰራዊቱ የኢትዮጵያን የአየር ክልል 24 ሰዓት ሙሉ በተጠንቀቅ እየጠበቀ መሆኑን የገለጹት ሌተናል ጀነራል ይልማ፤ አየር ኃይሉ በማንኛውም ሁኔታ ለግዳጅ ዝግጁ የሆነ ኃይል ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ሰራዊቱ በየቀኑ የመሳሪያ፣ የአካልና የእውቀት ፍተሻ በማድረግ የተሟላ ስነ-ልቦና ተላብሶ አገሩን እየጠበቀ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም