የተጀመረው የለውጥ ሂደት ውጤትን በተግባር እያሳየ ይቀጥላል - አቶ ርስቱ ይርዳው - ኢዜአ አማርኛ
የተጀመረው የለውጥ ሂደት ውጤትን በተግባር እያሳየ ይቀጥላል - አቶ ርስቱ ይርዳው
ሐዋሳ፣ ነሀሴ 5 ቀን 2014 (ኢዜአ) የተጀመረው የለውጥ ሂደት የሀገርን ብልጽግና ጉዞ ስኬት በተግባር እያሳየ በጽናት እንደሚቀጥል የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ተርባይን የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጨት መጀመሩን በማስመልከት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም ሀገራችን ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በብቃት እያለፈች ወደ ብልጽግና የጀመረችውን ጉዞ ትቀጥላለች ብለዋል።የተጀመረው የለውጥ ሂደት ውጤትን በተግባር እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
ጠላቶችን እያሳፈረ የፈተናዎች ብዛት ያልበገራት ሀገራችን በህዝቦቿና በጠንካራ ልጆቿ የላቀ ጥረት ተስፋ ሰጪ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ብዙዎችም ስለመበታተኗ በድፍረት ቢናገሩም የጠላትን ወጥመድ እየሰበርን አንድነታችንን እያጠናከርን መሄድ በመቻላችን የተስፋ ብርሀን ለማየት በቅተናል ሲሉ ገልጸዋል።
ያም ሆኖ በህዝቧና በለውጡ መንግስት ጽናትና አንድነት ማንም ወደሗላ እንደማይጎትታት በተግባር ማሳየቷን ቀጥላለች ያሉት አቶ ርስቱ ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞዋ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ህዝቦቿ በጥረት ከድህነትና ሗላ ቀርነት ተላቀው ለቀጣይ ትውልድ አኩሪ ቅርስ ማውረስ እንደሚችሉ እያረጋገጡ እንደሚገኙ በህዳሴው ግድብ ላይ ያሳየነው ጥረት ውጤት የዜጎቻችንን ተስፋ ያለመለመ ነው ብለዋል።
በሁሉም ዘርፍ ተጠናክሮ የቀጠለው ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዟችን ከግብ ደርሶ ዜጎቻችን ተጠቃሚነታቸው ከፍ የሚልበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ነው ያሉት።
ሀገራችን ኢትዮጵያም ፈተናዎችን በብቃት እያለፈች ወደ ብልጽግናዋ መገስገሷን ትቀጥላለች ያሉት አቶ ርስቱ፤ ለክልሉ ህዝብና ለመላው ኢትዮጵያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።