ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድቡ ኢትዮጵያዊያን ከተባበርን ችግሮቻችንን ማለፍ እንደምንችል ማሳያ ነው - አቶ ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ፣ ነሀሴ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያን ከተባበርን ችግሮቻችንን ማለፍና ወዳለምነው ግብ መድረስ እንደምንችል ማሳያ ነው ሲሉ የሲዳማ ብሄራዊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ የህዳሴ ግድብ 2ኛ ተርባይን ሀይል ማመንጭት መጀመሩን አስመልክቶ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልክዕታቸውም ግድቡ የአንድነት ማስተሳሰሪያ ገመዳችን፣ የጽኑነት ተምሳሌት፣ የሕብረ ብሔራዊ አንድነት አርማችን ነው ብለዋል።

ግድቡ የጋራ ዐሻራ ማህተም የረፈበት በላይ የትውልድ ማስተሳሰሪያ ሐውልት እንደሆነ ተናግረዋል።የግድቡ ኃይል ማመንጨት እውን እንዳይሆን ሲገዳደሩ የነበሩ ጠላቶችን ጫናና የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በመቋቋም ስኬት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

ይህን ሁሉ ተግዳሮት ለማለፍ በጥበብ የተሞላ ታላቅና አስደማሚ የዲፕሎማሲ ስራዎች መሰራታቸውን ያነሱት አቶ ደስታ፤ የተወጠነው ሴራ ሁሉ ከሽፎ ኢትዮጵያዊያን ለታላቅ ኩራትና ደስታ መብቃታቸውን ገልጸዋል።

ዛሬ አባይ የሚጨበጥ፥ የሚዳሰስና የሚታይ እውነታ ሆኗል በማለት ገልጸው፤ ግድቡ ኢትዮጵያን በብርሃን ሊያደምቃት፤ ለታላላቅ ኢንዱስትሪዎቻችን የማያልቅ የኃይል ምንጭ ሊሆን መዘጋጀቱ የዘመናት ቁጭትን የሚመልስ የዚህ ትውልድ የታሪክ ሰሪነት ምስጢር ነው ብለዋል።

የግድቡ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አስተዋጽኦ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም