አንድ ስንሆን፣ ስንተባበርና ስንተጋገዝ መስራትና ማሸነፍ እንችላለን - አቶ ፀጋዬ ማሞ - ኢዜአ አማርኛ
አንድ ስንሆን፣ ስንተባበርና ስንተጋገዝ መስራትና ማሸነፍ እንችላለን - አቶ ፀጋዬ ማሞ
ሚዛን አማን፣ ነሀሴ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) አንድ ስንሆን፣ ስንተባበርና ስንተጋገዝ መስራትና ማሸነፍ እንደምንችል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አረጋግጦልናል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ ገለጹ።
የግድቡን ሁለተኛ ተርባይን ሃይል ማመንጨት መጀመርን አስመልክቶ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ፀጋዬ፤ ግድቡ የኢትዮጵያን ከፍታ ያበሰረ፣ ለአንድ ዓላማ በጋራ መስራትና አንድነት ምን ያህል ውጤቱ ያማረ እንደሆነ የረጋገጠ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ያለውን ጥቂት ሀብት አዋጥቶ ሲሰራ፣ ሲለፋ እና ሲታትር በዚህ ደረጃ ለውጤት ሲደርስ ያየን የትውልድ አካል በመሆናችን ደስታችን ላቅ ያለ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ግድቡ እንዲደናቀፍ ብዙ ስራዎች በጠላቶቻችን ቢሰራም በጽናት አልፈን ፍሬውን ለመቅመስ በቅተናል ብለዋል።የግንባታ ስራው እንዲቋረጥ ዘርፈ ብዙ ዘመቻዎች ተከፍተውብን የተለያዩ ዓይነት ጫናዎች ተጭነውብናል ሲሉም ጠቅሰዋል።
እነዚህን ሁሉ ጫናዎች ሰብረንና አሸንፈን መውጣት የቻልነው ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶቻችንና መላው ህዝቡ የዲያስፖራው ማህበረሰብ በሰሯቸው ጠንካራ ስራዎች እንደሆነ ጠቁመዋል።
ድህነትን ለማሸነፍና ከችግር ለመውጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ይህ ግድብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።