የፍራፍሬ ልማት ፕጄክት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አይነተኛ ሚና ይጫወታል-አቶ ኡስማን ሱሩር

103

ሐዋሳ፤ ነሀሴ 05/2014 (ኢዜአ)፡ የአረንጓዴ አሻራ አካል የሆነው የፍራፍሬ ልማት ፕጄክት የደን ሽፋንና ሥነ ምህዳርን ከማሻሻል ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ተናገሩ።

የፌዴራልና የደቡብ ክልል  የስራ ሃላፊዎች በክልሉ  ጎፋ ዞን ቡልቂ ከተማ በመገኘት የ30-40-30 የአረንጓዴ አሻራ ፕሮጀክት አካል የሆነውን ችግኝ ተከላ ዛሬ አከናውነዋል።  

የቢሮው ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በዚህ ወቅት እንዳሉት  በክልሉ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የአረንጓዴ አሻራ አካል የሆነው የፍራፍሬ ልማት ፕሮጄክት የደን ሽፋንና ሥነ ምህዳርን ከማሻሻል ባሻገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አይነተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።

ዘንድሮ እንደ ክልል ለመትከል ከታቀደው 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን የተለያየ ጠቀሜታ ካላቸው ችግኞች ውስጥ እስካሁን 80 በመቶው መተከሉን ተናግረዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ዛሬ ላይ ሆነን ለነገ ትውልድ የምንሰራው መልካም ታሪክ በመሆኑ በርብርብ ልናከናውነው ይገባል ብለዋል ።

በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌን ጨምሮ የፌዴራልና የክልሉ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በቡልቂ ከተማ ግንባታው እየተከናወነ በሚገኘው የቴክክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ቅጥር ግቢ በተካሄደው የችግኝ  ተከላው መርሐ ግብር ላይ የአከባቢው ነዋሪዎችም ጭምር ተሳትፈዋል።

በደቡብ ክልል የ30-40-30 የአረንጓዴ አሻራ ፕሮጀክት ተቀርፆ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን በፕሮጀክቱ በመንግስት ተቋማት ውስጥ በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ100 እስከ 10 ሺህ የፍራፍሬ ችግኞች ይተከላሉ።

 በመጀመሪያ ዓመት 30 በመቶው በቀጣይ ባሉት ዓመታት ደግሞ 40 እና 30 በመቶው በተከታታይ ዓመታት እንደሚተከል አቅጣጫ ተቀምጦ ተግባራዊ እየሆነ መሁኑ ተመላክቷል።

የሥራ ሃላፊዎቹ ቀደም ሲል በቡልቂ ከተማ ግንባታው የተጠናቀቀውን የመንገድ ፕሮጄክት መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ማድረጋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም