በኢትዮጵያ ለተጠለሉ ስደተኞች የሰብአዊ ድጋፍ እጥረት እንዳያጋጥም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

83

ነሐሴ 05 ቀን 2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ለተጠለሉ ስደተኞች የሰብአዊ ድጋፍ እጥረት እንዳያጋጥም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የኢትዮጵያ ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ጥሪ አቀረበ።

የስደትና መፈናቀል ምጣኔ በጨመረበት አሁናዊ የዓለማችን ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናም ቀውሱ ተባብሶ ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተስፋሁን ጎበዛይ እንደሚሉት፤ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የስደተኞች አሀዝ ወደ 5 ሚሊዮን አሻቅቧል።

በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ገጥሟቸው ወይም ጥቃት ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ስደተኞችን እየተቀበለች መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ በስድስት ክልሎች በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ከ870 ሺህ በላይ ስደተኞችን ማስጠለሏን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ የነበሩ ስደተኞችም በሰሜን ጐንደር ዳባት በተቋቋመው ጣቢያ መዛወራቸውን ተናግረዋል።

ስደተኞችን በተመለከተ ተቀባይ አገራት፣ የመንግስታቱ ድርጅት ኤጀንሲዎችና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተቀባይ አገራትን ጫና የመጋራት መርህ መሰረት የጋራና ተናጠላዊ ኅላፊነት እንደለባቸው ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያም እንደ ተቀባይ አገር የስደተኞች ምላሽ ማዕቀፉን በማዘጋጀት፣ የመጠለያ ቦታዎችን የመስጠትና ለስደተኞች የደህንነት ዋስትና በመስጠት ሃላፊነቷን እየተወጣች ነው ብለዋል።

27 የስደተኞች መጠለያ ጣቢዎችን በመገንባት የመጠለያ ቦታዎች በነፃ የማቅረብና ዓለም አቀፍ ስደተኞችን አያያዝ የሕግ ማዕቅፍ በማውጣት የበኩሏን ሚና ተወጥታለች ነው ያሉት።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽንና መሰል ዓለም አቀፍ አጀንሲዎች ስደተኞችን መደገፍ፣ የተቀባይ ማህበረሰብን ኢኮኖሚያዊ ጫና የመሸከም ብሎም የሶስተኛ አገር አቋራጭ መንገድ የማመቻቸት ሃላፊነት እንደሚወጡ ገልጸዋል።

ተቋማቱ በፖለቲካ ገለልተኝነት በኩል የራሳቸው ውስንነቶች እንዳለ ሆኖ ከረጂ አካላት ስደተኞችን በመደገፍ ከአገልግሎቱ ጋር በቅንጅት ሲሰሩ መቆየታቸውን አንስተዋል።

ከሁለት ዓመታት ወዲህ ግን ኮቪድ 19 ወርርሽኝ ክስተትና የስደት ምጣኔ ባለመሻሻሉ በተፈጠረ መሰላቸት ድርጅቶቹ ከረጂ አካላት አሰባስበው በቂ ድጋፍ እያቀረቡ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ለአብነት በዓለም ምግብ ፕሮግራም ይቀርብ የነበረ የምግብ ድጎማ አቅርቦት መጠን በ50 በመቶ መቀነሱን ተናግረዋል።

ድርጅቶቹ ካላቸው ሀብት ውስንንት አኳያ የወቅቱ ውስን አቅርቦትም ቀጣይነቱ ዋስትና እንደሌላቸው ስለመግለጻቸው ተናግረዋል።

ይህም ስደተኞችን ለሌላ አላስፈላጊ ድርጊት እንዲሳተፉ ስለሚያነሳሳ ብሎም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ስደተኞች ለረሃብ እንዳይጋለጡ በአገልግሎቱና በኤጀንሲዎች በኩል ከወዲሁ የድጋፍ ጥሪ ተደርጓል ብለዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ኤጀንሲዎች ስደተኞችን ብቻ ሳይሆን ስደተኞች ተቀባይ ማህበረሰብ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ድጋፍ ማድረግ ኅላፊነት ቢኖርም ከጊዜ ወደ ጊዜ ክፍተት እየተስተዋለበት ነው ብለዋል።

በሶማሌ ክልል 'መልከዲዳ' የስደኞች መጠለያ ጣቢያ ተቀባይ ማህበረሰብና ስደተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተገነባውን የመስኖ ፕሮጀክት በአርዓያነት ጠቅሰው፤ መሰል ፕሮጀክቶች ሊሰፉ ይገባል ነው ያሉት።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከአፍሪካ በሚገኙ ከፍተኛ ቁጥር ካላቸው ስደተኞች እና የሌሎች አህጉራት ስደተኞችን በእኩል ሚዛን ትኩረት እየሰጠ እንዳልሆነ የዩክሬን ስደተኞችን ለአብነት አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞችን የወቅቱ ሰብዓዊ ርዳታ ፍላጎት ማሟላትና በአግባቡ መምራት ካልተቻለ ለፀጥታ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ቀውሶች እንደሚያስከትል ገልጸዋል።

ይህም ለመንግስት ብቻ ሳይሆን ለስደተኞችና ለተቀባይ ማህበረሰብም ችግር የሚዳርግ በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶ ስደተኞች የተደቀነባችውን ችግር ሊቀርፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም