በወለድ አልባ የፋይናንስ ሥርዓት ተደራሽነት 117 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ተቀማጭ ማድረግ ተችሏል - አህመድ ሺዴ

85

ነሐሴ 5/2014(ኢዜአ) በወለድ አልባ የፋይናንስ ተቋማት ተደራሽነት ከ11 ሚሊየን በላይ በሚሆን ሂሳብ 117 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ተቀማጭ ማድረግ መቻሉን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ገለጹ።

በኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተሰናዳው ሀገር አቀፋ ከወለድ ነፃ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ጉባኤ  "አካታች  የፋይናንስ  አገልግሎት  በኢትዮጵያ  ተደራሽ  ማድረግ"  በሚል መሪ ሐሳብ ተካሂዷል።

በጉባኤው ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ፣ የፋይናንስ ሥርዓት ተደራሽነትን ለማስፋት ሰፊ የአሰራርና የሕግ መሻሻል መደረጉን ገልጸዋል።

የሙስሊም ማኅበረሰብ የፋይናንስ ተደራሽነት ለማሳደግም የወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎት፣ የእስላሚክ መድንና ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች እንዲቋቋሙ የሚያደርግ የሕግ ማሻሻያ መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ወስደው አራት ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች ስራ መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

የወለድ አልባ የፋይናንስ ተቋማትን ተደራሸ ለማድረግ በተከናወነ ተግባርም ከ11 ሚሊየን በላይ በሚሆን ሂሳብ 117 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ተቀማጭ ተደርጓልዕ ብለዋል።

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ፤ በዓለም ላይ በወለድ አልባ የፋይናንስ ሥርዓት ከ2 ትሪሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገንዘብ እንደሚንቀሳቀስ ገልጸዋል።

አገልግሎቱም በፍጥነት እያደገ መሆኑን ጠቅሰው፤ እንግሊዝና ጎረቤት አገር ኬንያ ግንባር ቀደም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ አገራት መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያም የሕግ ማዕቀፍ በማውጣት በቂ ልምድ እስኪገኝ ድረስ ባንኮች ወለድ አልባ የመስኮት አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውን  አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ ኢድሪስ፤ የፋይናንስ ሥርዓቱ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ የመንግስትን ጠንካራ ሚና አንስተዋል።

የፋይናንስ ሥርዓቱን ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ የማሻሻያ ሥራ በማከናወን ለውጥ ማምጣት እንደተቻለም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን በፋይናንስ ሥርዓቱ ላይ እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው ተደርጓል ብለዋል።  

የዒድ እስከ ዒድ መርሃ-ግብር ጣምራ ሰብሳቢ ዑስታዝ አቡበከር አህመድ፤ ከቅርብ አመታት ወዲህ በፋይናንስ አገልግሎቱ ሁሉንም የሚያሳትፍ አሰራር ተዘርግቶ እውን መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመፍጠር ቀላል የማይባል ዋጋ ስለመከፈሉ አስታውሰው ለዚህ ስኬት መብቃቱን ተናግረዋል።

በመድረኩ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት ያለው ዕድልና ዕጣ-ፈንታ፣ የሸሪዓ አስተዳደር፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ የፋይናንስ ሥርዓት እና ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት በሚል ርዕሰ-ጉዳይ ላይ የተሰናዱ ጥናታዊ ጹሑፎች ቀርበው ምክክር ተካሂዶባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም