ግድባችን ሁለተኛው ተርባይን ሀይል ማመንጨቱ ከጨለማ ወደ ብርሃን ለመውጣት መቃረባችንን የሚያሳይ ነው- የሶማሌ ክልል

66

ጅግጅጋ ፤ ነሐሴ 5/2014(ኢዜአ) ግድባችን ሁለተኛው ተርባይን ሀይል ማመንጨት መጀመሩ ከጨለማ ወደ ብርሃን ለመውጣት የጀመርነው ጥረት መቃረቡን የሚያሳይ ነው ሲሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ህዝባዊ ተሳትፎ የክልሉ አስተባባሪ ገለጹ።

የሶማሌ ክልል ነዋሪዎች እስካሁን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ  ከ342 ሚሊዮን  ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውም ተመልክቷል ።

አስተባባሪው አቶ አብዲረዛቅ ሼህ አብዲራህማን ሰይድ ዛሬ ሁለተኛው ተርባይን ስራ መጀመሩን አስመልክተው የእንኳን ደስ አለን መልዕክትም አስተላልፈዋል።

ግድቡ በዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ ከጨለማ ወደ ብርሃን ለመውጣት የጀመርነው ጥረት መቃረቡን የሚያሳይ ነው ፤ ለክልላችን አብዛኛው ከተሞች የሀይል አቅርቦት እንዲያገኙ ያስችላል" ብለዋል።

ለግድቡ ግንባታ እውን መሆን የክልሉ ነዋሪዎች በቦንድ ግዥ፣ በስጦታና በድጋፍ እስካሁን 342 ሚልዮን 221ሺህ 715  ብር ድጋፍ ማድረጋቸውንም አመልክተዋል።

ከመነሻው ጀምሮ እስካሁን የደረሰበት ደረጃ አርብቶ አደሩ ከሚያረባቸው እንስሳት ፣ ሠራተኞች ከደመወዛቸው ፣ባለሀብቶች ቦንድ በመግዛት የግድቡ ባለቤት መሆናቸውን በተግባር ማሳየታቸውንም ጠቅሰዋል።

የክልሉ ህዝብም የግድቡ ግንባታው እስኪጠናቀቅ በተለያየ መልክ የጀመረው ተሳትፎና ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል ።

የኢትዮጵያዊን የትብብር፣ የልማትና የአንድነት ማሳየ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ተርባይን ስራ መጀመሩ ለመላው ኢትዮጵያዊያንና ለግንባታው መሳካት ቀን ከሌሊት እየደከሙ ላሉ  ባለሙያዎች በክልሉ ህዝብ ስም የእንኳን ደስ አለን መልዕክት አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም