ለዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት፣ ለኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት የሲቪል ማህበራት ጠንካራ ተሳትፎ ወሳኝ ነው- ዶክተር አለሙ ስሜ - ኢዜአ አማርኛ
ለዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት፣ ለኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት የሲቪል ማህበራት ጠንካራ ተሳትፎ ወሳኝ ነው- ዶክተር አለሙ ስሜ
ነሐሴ 05 / 2014 (ኢዜአ) ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት፣ ለኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት የሲቪል ማህበራት ጠንካራ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር አለሙ ስሜ ገለጹ።
''የጎለበተ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ተሳትፎ ለሀገር ግንባታ'' በሚል መሪ ሃሳብ ከመንግሥት አካላት የተውጣጡ ኃላፊዎችና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ተወካዮች ምክክር አድርገዋል።
የሲቪል ማህበራት ከለውጡ በፊት የነበራቸው ተሳትፎ፣ ከመንግሥት ጋር የሚሰሩበት አግባብ እንዲሁም ከለውጡ በኋላ ያላቸውን ተሳትፎ በተመለከተ በመድረኩ ተነስቷል።
ከዚህ ቀደም በነበረው አካሄድ መንግሥትና የሲቪል ማኅበረሰብ በጋራ ከመሥራት ይልቅ በተለይ በዴሞክራሲ፣ በሰብአዊ መብትና በግጭት አፈታት ዙሪያ በተቃርኖ የቆመ ስለመሆኑ ተመላክቷል።
ከለውጡ በኋላ ግን መንግሥትና የሲቪል ማህበራት በሁሉም መልኩ ተቀራርበው በጋራ እየሰሩ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር አለሙ ስሜ ገልጸዋል።
የሀገሪቷ የዴሞክራሲ ሽግግር፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት እውን የሚሆነው በሲቪል ማህበራት እገዛ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ለዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት፣ ለኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት በመንግሥት ጥረት ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ የሲቪል ማህበራት ጠንካራ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የሲቪል ማህበራት ሲመራበት የነበረውን ሕግ በማሻሻል ምቹ የአሰራር ሂደቶች እንዲፈጠሩ በመደረጉ አጠቃላይ ለሀገራዊ ለውጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብለዋል።
በዚህም ባለፉት አራት የለውጥ ዓመታት የሲቪል ማህበራት ለሀገር ያበረከቱት አስተዋጽኦ ሰፊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንኑ መልካም ጅምራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ፣ ከዚህ ቀደም የነበረው የሕግ ማዕቀፍ የሲቪል ማህበራት ብዙም እንዳይሰሩ ማድረጉን አስታውሰዋል።
ከለውጡ ወዲህ በተደረገው ማሻሻያ ግን ምቹ የሥራ ሁኔታዎች ተፈጥረው ከመንግሥት ጋር በትብብር እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
በቀጣይም ለሀገሪቷ የዴሞክራሲ ሽግግር፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ካሉት 3 ሺህ 928 የሲቪል ማህበራት መካከል 3 ሺ 427ቱ አገር በቀል ሲሆኑ ቀሪዎቹ የውጪ ሀገራት ናቸው፡፡
የሲቪል ማህበራቱ 13 ሚሊዮን ዜጎችን በቀጥታ ተጠቃሚ ሲያደርጉ ለ7 ነጥብ 9 ሚሊየኑ ደግሞ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑ ታውቋል።