ቀጥታ፡

ሁለተኛው ተርባይን ሃይል ማመንጨቱ ኢትዮጵያውያንን በራሳቸው መልማት እንደሚችሉ ለአለም ያሳየ ነው - የአሶሳ ነዋሪዎች

አሶሳ፤ ነሐሴ 05 / 2014(ኢዜአ) ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ሃይል ማመንጨት መጀመሩ ኢትዮጵያውያን በአንድነትና በራሳቸው አቅም መልማት እንደሚችሉ ለዓለም ያሳየ መሆኑን በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የህዳሴው ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ዛሬ ስራ መጀመርን አስመልክቶ ኢዜአ ካነጋገራቸው የአሶሳ ነዋሪዎች መካከል አቶ ኢብራሂም አዙቤር ፤ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ወደ ፍጻሜ መቃረብ የኢትዮጵያውያንን አንድነት በግልጽ ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱን የህልውናችን መገለጫ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በራሷ መልማት እንደምትችልም ግድቡ አረጋግጧል ያሉት ነዋሪው፤ የአፍሪካን ጨምሮ ለሌሎች የዓለም ሃገራት ምሳሌ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያውያን ስለህዳሴው ግድብ የሚያስቡት ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ካልሆነ በቀር ሌላ ስጋት በፍጹም አይገባንም ነው ያሉት አቶ ኢብራሂም፡፡

ወይዘሮ አልካኔል ኦላሳ በበኩላቸው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተደቀኑበትን ፈተናዎች ሁሉ እያለፈ ለዚህ መብቃቱ በኢትዮጵያዊነቴ እንድኮራ አድርጎኛል ብለዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ ደመወዜን ጨምሮ በርካታ ድጋፎችን አድርጊያለሁ፤  ህብረተሰቡንም በመቀስቀስ ድጋፉን እንዲያጠናክር ሳደርግ ነበር፤  ድጋፌ ተጠናክሮ ይቀጥላል፤ በፈጣሪ እገዛ ጭምር የህዳሴውን ግድብ እናጠናቅቃለን ሲሉ በቁጭት ገልጸዋልል፡፡

የ12ኛ ክፍል ተማሪዋ መናህል አብዱራህማን ፤ የህዳሴው ግድብ የሃገራችን የሃይል ፍላጎት በማሟላት ሁለንተናዊ አቅም እንደሚሆን ያለን ተስፋ እውን መሆኑን አሳይቷል ስትል ተናግራለች፡፡

በዚህም በእጅጉ ደስተኛ ነኝ ብላለች፡፡

ፕሮጀክቱን ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ሳደርግ ነበር፤ እስኪጠናቀቅ የአቅሜን ያህል መደገፌን እቀጥላለሁ ስትል ለኢዜአ ገልጻለች፡፡

ከአባይ ወንዝ የሚገባንን ሳንጠቀም በቁጭት የኖርንበት ዘመን አብቅቷል ያሉት ደግሞ አቶ አያንሳ ዋቅጅራ  ናቸው፡፡

ፕሮጀክቱ የሃገራችንን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ በመደገፍ ወደ ተሻለ ደረጃ በማሸጋገር ከድህነት ያወጣናል ብለዋል፡፡

የሃገር ውስጥ እና የውጭ ጠላቶቻችን ፕሮጀክቱን ለማደናቀፍ ባደረጉት ጥረት በመተከል እና አካባቢው የተከፈለው የህይወት መስዋእትነት ያስታወሱት ነዋሪው፤ ይህም በቁጭት እንድንሰራው አድርጎናል ብለዋል።

 እየተረጋጋ የመጣውን የመተከል ዞን ሠላም ከማስቀጠል ባለፈ በግሌ ለፕሮጀክቱ የማደርገውን ድጋፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክሬ እቀጥላለሁ ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም